ሱዳን፡ በጎርፍ የተነሳ ቢያንስ 90 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

በጎርፍ የተጥለቀለቀ መንደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሱዳን በጎርፍ ምክንያት 90ያህል ሰዎች ሲሞቱ 400 ሺዎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ እና ከ100 ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁናቴ የናይል ወንዝ ሞልቶ 17.5 ከፍ በማለቱ ጎርፉ ሊከሰት ችሏል።

ድርጅቱ አክሎም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ በጎርፉ የተነሳ ይህም ተስተጓጉሏል ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያደረገው ዳሰሳ እንደሚያሳየው በጎርፉ ምክንያት ወደ 2 ሺህ የውሃ መገኛ ስፍራዎች ተበክለዋል ወይንም ተሰብረዋል።

በጎርፉ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ክልሎች ምስራቅ ሱዳን፣ ነጭ ናይል፣ ዳርፉር፣ እና ካርቱም ሲሆኑ የተፈናቀሉ ሰዎች በአፋጣኝ የመጠለያና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

" እሁድ እለት በካርቱም ብቻ፣ ከ21,000 ሰዎች በላይ በጎርፍ ተጎድተዋል። መንግሥትም በካርቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል። በመላ አገሪቱ ከነሐሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ 380 ሺህ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ሲጎዱ 90 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።" ያሉት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ቃል አቀባይ ዤንስ ላይርኬ ናቸው።

በጎርፉ የተነሳ መንገዶች በመበላሸታቸው አስቸኳይ የሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተጎጂዎች ማድረስ አልተቻለም።