ኮሮናቫይረስ ፡ ስፔን ክትባት አንወስድም የሚሉ ዜጎችን ልትመዘግብ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኮሮናቫይረስ ክትባት አንወስድም የሚሉ ዜጎችን እንደምትመዘግብ ስፔን አስታወቀች። ዝርዝሩን ለሌሎች የአውሮፓ አገሮች እንደምትሰጥም ተገልጿል።
የጤና ሚንስትሩ ሳልቫዶር ኢላ እንዳሉት፤ ይህ ዝርዝር ለሕዝቡና ለቀጣሪዎች ይፋ አይደረግም።
“ቫይረሱን ማሸነፍ የሚቻከው ሁላችንም ስንከተብ ነው” ብለዋል ሚንስትሩ።
ከአውሮፓ አገሮች መካከል በቫይረሱ ክፉኛ ከተጎዱት አንዷ ስፔን ናት። ባለፈው ሳምንት በአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ፍቃድ ያገኘውን የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት መስጠትም ጀምራለች።
የጤና ሚንስትሩ ክትባቱን መውሰድ ግዴታ አይደለም ካሉ በኋላ “አንወስድም የሚሉ ሰዎችን ግን እንመዘግባለን። ዝርዝሩን ለአውሮፓውያን አጋሮቻችን እንሰጣለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
የዜጎችን የግል መረጃ ለመጠበቅ ሲባል ዝርዝሩ ለሕዝብ ይፋ እንደማይደረግ አያይዘው ተናግረዋል።
በቅርቡ በተሠራ ዳሰሳ መሠረት ክትባት አንወስድም ያሉ ስፔናውያን ቁጥር ጥቅምት ላይ ከነበረው 47% ወደ 28% ወርዷል።
ክትባቱን ለመውሰድ ተራቸው የደረሰ ዜጎች በየግዛታቸው በኩል መረጃ እንደሚደርሳቸው ሚንስትሩ አስረድተዋል።
“ክትባት አንወስድም የሚሉ ሰዎች ትክክል እንዳልሆኑ ብናምንም አልወስድም ማለት መብታቸው ነው። የሰዎችን ጥርጣሬ ለማስወገድ እንሞክራለን። መከተብ ሕይወትን ይታደጋል። ከወረርሽኙ ልንላቀቅ የምንችለው በክትባት አማካይነት ነው” ብለዋል።
በስፔን በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ከ50,000 በላይ ሆነዋል። 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ተይዘዋል።
በስፔን ከምሽት 5፡00 እስከ ንጋት 12፡00 ድረስ ብሔራዊ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥላለች።
ዜጎች ከቤት መውጣት የሚፈቀድላቸው ወደሥራ ለመሄድ፣ መድኃኒት ለመግዛት እንዲሁም አረጋውያንና ሕፃናትን ለመንከባከብ ብቻ ነው።












