በናይጄሪያ ትምህርት ቤት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ጠፍተዋል ተባለ

የትምህርት ቤት ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Gail Kankara

በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኝ ትምህርት ቤት ጥቃት መድረሱን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች መጥፋታቸው ተገልጿል።

ታጣቂዎች በሞተርሳይክል ተጭነው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ከደረሱ በኋላ ወደ ሰማይ መተኮስ እንደጀመሩና በርካቶችም በፍራቻ ብትንትን ብለው ከአካባቢው እንደጠፉ የአይን እማኝ ተናግሯል።

ካትሲና ግዛት የሚገኘው የመንግሥት አዳሪ ትምህርት ቤት 800 ተማሪዎች ያሉበት ሲሆን ከበባውም የደረሰው አርብ አመሻሹ ላይ ነው።

በትናንትናው ዕለት የናይጄሪያ ጦር ታጣቂዎቹ የተደበቁበትን ስፍራ እንዳገኘውና ከሰራዊቱ አባላትም ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደነበርም ተገልጿል።

በትምህርት ቤቱ ደረሰ በተባለው ከበባም ሆነ ጥቃት የደረሰው ጉዳት ግልፅ ባይሆንም ባለስልጣናቱ ግን ጉዳት ደርሶበት የመጣ ተማሪ የለም ብለዋል።

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ጥቃቱን አውግዘው የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥልና ምን ያህል ተማሪዎችም በትክክል እንደጠፉ ቆጠራ እንዲካሄድም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ልጆቻቸውን በአፋጣኝ ከትምህርት ቤት የወሰዱ ወላጆችም የትምህርት ቤቱን ባለስልጣናት እንዲያሳውቁም ተብለዋል።

የወንዶች ብቻ አዳሪ ትምህርት ቤት በሆነው ትምህርት ቤት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችም ተኩስ ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ እንደሰሙና ለአንድ ሰዓትም የዘለቀ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ፖሊስ በቦታው ከመድረሱ በፊት ታጣቂዎቹን መግታትም እንደቻሉ ባለስልጣናቱ አስረድተዋል።

በትናንትናው ዕለትም በነበረው መግለጫ ፖሊስ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ገልፆ የተወሰኑትም ታጣቂዎች መሸሻቸውም ተነግሯል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ተማሪዎቹ ለደህንነታቸው በመስጋት አጥር እየዘለሉ ከግቢው ወጥተዋል።

ሸሽተው ከነበሩት መካከል 200ዎቹ ቢመለሱም በርካታ ተማሪዎች በታጣቂዎቹ ታግተው እንደተወሰዱ የአይን እማኞቹ ተናግረዋል።

አንድ ፖሊስም ቆስሎ ሆስፒታል ገብቶ ህክምና እየተደረገለት መሆኑንም መግለጫው አክሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር በመጣመር የጠፉትን ተማሪዎች እየፈለጉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ወላጆች ግን ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤቱ አስወጥተዋል።

"ትምህርት ቤቱ ባዶ ሆኗል፣ ሁሉም ተማሪዎችም ግቢውን ለቀው ወጥተዋል" በማለት ኑራ አብዱላሂ የተባለ የአይን እማኝ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግሯል።

"ከግዛቲቷ ወጥተው የነበሩ አንዳንድ ተማሪዎች ዛሬ ቢመለሱም በርካቶቹ በአውቶብስ ተሳፍረው ወደ መኖሪያ ቀያቸው አምርተዋል" ብሏል።

የካትሲና አስተዳዳሪ አሚኑ ቤሎ ማሳሪ በግዛቲቷ የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሙሉ እንዲዘጉ ወስነዋል።

በጎሮጎሳውያኑ 2014 ከቺቦክ ግዛት 270 ሴት ተማሪዎች በፅንፈኛው ቦኮ ሃራም ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

ካትሲና ትምህርት ቤት ላይ ለደረሰው ከበባም ሆነ ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። አካባቢው ቦኮ ሃራም ከሚንቀሳቀስበት ራቅ ያለም ነው ተብሏል።