ሞባይል ፡ ስልኮቻችንን ለምን በተደጋጋሚ እንነካካለን? ተመራማሪዎች ምላሽ አላቸው

ስልኳን እየተመለከተች ያለች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብዙ ሰዎች ስልኮቻቸውን ይነካካሉ፤ በጣም በተደጋጋሚ። ለምን እንደዚያ እንደሚያደርጉ ቢጠየቁ ግን ምላሻቸው ለራሳቸውም አጥጋቢ ላይሆን ይችላል። ስልኮቻችንን ከኪሳችን ወይም ከቦርሳችን መዥረጥ አድርገን በየደቂቃው እንመለከታለን።

ይህን የምናደርገው የጽሑፍም የድምጽም ጥሪ ደርሶን አይደለም። አንድ በዚህ ረገድ የተደረገ ጥናት ሰዎች ስልካቸውን የሚነካኩበት አግባብ፣ አንድን የሚጠበቅ ነገር በመሻት ወይም የድምጽም ሆነ የጽሑፍ መልዕክት ስላላቸው አይደለም ይላል።

እንዲያውም የስልክ ንክኪ ሱስ እንጂ አንድን የታወቀ ነገር በመፈለግ የሚደረግ አይደለም ሲል ጥናቱ ይደመድማል። የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ባጠናውና ደረስኩበት ባለው ምርምር 89 ከመቶ የስልክ ንክኪዎች የሚፈጠሩት ምንም ዓይነት የድምጽም ሆነ የጽሑፍ ጥሪ ሳይደርሰን ነው።

11 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው የኢሜልም ይሁን ሌላ የጽሑፍ ጥሪ ደርሷቸው ወይም አግባብነት ያለው የስልክ ጥሪ ለማድረግ ስልካቸውን የሚነኩት። ጥናቱ ሌላ ደረስኩበት ያለው ነገር ከሰዎች ጋር የምናደርገው የጽሑፍ መልዕክት ልውውጥ (ቻት) ለጭንቀት እንደሚዳርግ ነው።

በተለይም የቡድን ቻት በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎችን ጠንከር ላለ ጊዜያዊ የአእምሮ ውጥረት ዳርጓቸዋል። በፌስቡክና በኢኒስታግራም ላይ ቁልቁል እየፈተሹ ሁሉን የመቃኘት አባዜ (Scrolling) ብዙዎች አዲስ ነገር ከታች እናገኛለን በሚል ረዥም ጊዜን በገጾቹ እንዲያጠፉ እንዳደረጋቸውም ጥናቱ አመላክቷል።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት አንድ የሲጋራ ሱሰኛ ከኪሱ ሲጋራ መዥረጥ አድርጎ እንደሚያወጣው ሁሉ፣ 89 ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች ስልኮቻቸውን ከኪሶቻቸው/ከቦርሳዎቻቸው የሚያወጡት በትክክል አንድን የሚጠበቅ ነገር ፈልገው ሳይሆን ሱስ ሆኖባቸው ነው።

ጥናቱ የተደረገባቸው ሰዎች ላይ በካሜራ ክትትል ሲደረግባቸው

የፎቶው ባለመብት, LSE

የምስሉ መግለጫ, ጥናቱ የተደረገባቸው ሰዎች ላይ በካሜራ ክትትል ሲደረግባቸው

በጥናቱ ላይ የተሳተፉት በዩናይትድ ኪንግደም፣ በጀርመንና በፈረንሳይ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። በተከታታይ ቀናት የስልክ ባህሪያቸው ምልከታ ተደርጎበታል። ዕለታዊ የስልክ ባህሪያቸውን የሚቀርጽ ካሜራም ተገጥሞላቸው ነው ጥናቱ የተደረገባቸው።

ይህ ጥናት የተደረገባቸው ሰዎች 22 ከመቶ ዋትስአፕ ለማየት ስልካቸው በርብረዋል፣ ሌሎች 17 ከመቶ የሚሆኑት ስልካቸው ስክሪን ላይ መልዕክት ካለ ብለው ፈትሸዋል። ወደ ሌላ ሰው ጥሪ ለማድረግ ስልካቸውን ደጋግመው ያወጡት 1 ከመቶ እንኳ አይሆኑም ተብሏል።

ከሰዎች ጋር ቻት ለማድረግ ስለሚመልሱት መልስና የቃላት አግባብነት አእምሮ ጭንቀት ውስጥ እንደሚከታቸው የተደረሰበት ቢሆንም ቻት ላይ ያሉ የጽሑፍ ልውውጥ መልዕክቶች ይዘት ለሕይወት ጠቃሚ ፋይዳ ያላቸው ሆነው አልተገኙም። ሰዎች ከወዳጆቻቸው ጋር ሲሆኑ ስልክን የመበርበር አባዜያቸው በመጠኑም ቢሆን ቀንሶ ታይቷል።

ብቻቸውን የተቀመጡ ሰዎች ወይም በትራንስፖርት ላይ ያሉ ሰዎች ግን በተደጋጋሚ ስልካቸውን እንደተመለከቱ ተስተውለዋል። ስልካቸውን በተደጋጋሚ የሚቃኙበትን ምክንያት ግን እነሱም እርግጠኞች አይደሉም።

ዕለታዊ የስልክ ባህሪያቸው እንዲቀረጽ የፈለጉና ጥናቱ የተካሄደባቸው ሰዎች መልሰው ከስልካቸው ጋር የነበራቸውን ባህሪ በቪዲዮ ተቀርጾ ሲመለከቱ ራሳቸውን ማመን እንዳቃታቸውና በጥናቱ ውጤት እጅጉኑ መገረማቸው ተነግሯል።

"እኔ በፍጹም ስልክ ሱሰኛ አድርጌ ራሴን አላይም ነበር። ስልኬን የማይበት ፍጥነትና ለምን ደጋግሜ እንደማየው ራሱ አይገባኝም። ያን ማድረጌ ራሱ ትዝ አይለኝም" ብለዋል ከተሳታፊዎቹ አንዷ።

ጥናቱን ከመሩት ሰዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሳአዲ ላህሉ "ስልክን ደጋግሞ መመልከት ልማድ ወይም ሱስ እንጂ ከድርጊትና ፍላጎት ጋር ቀጥታ ግንኙነት የለውም" ይላሉ።

ስልክን ደጋግሞ የማየት፣ የመነካካት ባህሪ ዓለም አቀፋዊ ችግር ሆኗል። በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቡና ጫና እያደረሰ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

ፕሮፌሰሩ ይህንን ሱስ ለማሸነፍ እንደ ነፍጥ አንጋቢ "ካውቦዮች" አንድ ሥርዓት ማበጀት አለብን ይላሉ። "ካውቦዮች ወደ ሳሎን ሲገቡ ሽጉጣቸውን ደጅ አስቀምጠው ነው።

"እኛም ስልኮቻችንን ከእኛ አርቀን ማስመጥ ባህል ማድረግ ሊኖርብን ይገባል፤ ቢያንስ ለተወሰነ ሰዓት" ይላሉ። ብዙ ሰዎች ስልኮቻቸውን በየደቂቃው ካላዩ ዓለም ጥላቸው የምትጠፋ ይመስላቸዋል።

"ምንም ነገር የትም አይሄድም፤ ባለበት ያዘግማል እንጂ፤ የሚያመልጡን ነገሮች ካሉም በሕይወታችን ያን ያህል ቦታ የምንሰጣቸው ነገሮች አይደሉም፤ ይመስሉናል እንጂ" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰአዲ።