የዓለም አትሌቲክስ ሽልማት፡ ሁለት አፍሪካዊያን ለዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌቶች ሽልማት ታጩ

ለተሰንበት ግደይና ፔረስ ጀፕቺርቺር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም አትሌቲክስ በየዓመቱ በሚያዘጋጀው ምርጥ ሴት አትሌቶች ሽልማት ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ እና ኬንያዊቷ ፔረስ ጀፕቺርቺር ከመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች ዝርዝር ውስጥ መግባታቸው ተገለፀ።

የዓለም አትሌቲክስ ማክሰኞ እለት በአስሩ ዝርዝር ውስጥ ገብተው ከነበሩ አትሌቶች አምስት ለመጨረሻው ዙር መመረጣቸውን አስታውቋል።

ሌሎች ሦስት አፍሪካዊያን አትሌቶች አስሩ ዝርዝር ውስጥ ተካተው የነበረ ቢሆንም 5ቱ ዝርዝር ውስጥ ግን መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል። እነዚህ አትሌቶች ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ፣ ኬንያዊያኖቹ ዶ ፌዝ ኪፕየጎን እና ሔለን ኦቢሪ ናቸው።

ሌሎቹ በአምስቱ ዝርዝር ውስጥ መካተት ያልቻሉት አትሌቶች ደግሞ የኔዘርላንዷ ፌምኬ ቦል እና እንግሊዟ ላውራ ሙር ናቸው።

የዘንድሮው ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ሽልማት ሥነ ሥርዓት በቨርቹዋል [ኢንተርኔት] በአውሮፓዊያኑ ታህሳስ 5 የሚካሄድ ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያም በቀጥታ ይሰራጫል ተብሏል።የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት 5ቱ እጩዎች

  • ለተሰንበት ግደይ- ኢትዮጵያ

ለተሰንበት ግደይ በ5000 ሜትር በ14፡06፡62 በመግባት የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብራለች። ቫሌንሺያ በተደረገው በዚህ ውድድር በጥሩነሽ ዲባባ ለአስራ ሁለት ዓመታት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሽላለች ተብሏል።

የ22 ዓመቷ ሯጭ የገባችበት ሰዓትም 14 ደቂቃ ከ6.62 ሰኮንዶች ሲሆን የጥሩነሸ ደግሞ 14 ደቂቃ ከ11.15 ሰከንዶች ነበር።

በሞናኮ በተካሄደው በዋንዳ ዲያመንድ ሊግም 5000 ሜትር ሩጫ በሁለተኛ ደረጃነት አጠናቃለች።

  • ሲፋን ሐሰን - ኔዘርላንድስ

ሲፋን ሐሰን 18,930 ሜትር በአንድ ሰዓት ጊዜ በመሮጥ የዓለም ክብረ ወሰን ይዛለች።

በ10 ሺህ ሜትር በ29፡36፡67 በማጠናቀቅም የአውሮፓ ክብረወሰን ያስመዘገበች ሲሆን በታሪክ አራተኛዋ ፈጣኗ ሯጭ ተብላለች።

  • ፔረስ ጀፕቺርቺራ- ኬንያ

የዓለም ግማሽ ማራቶን አሸናፊ ናት። በሴቶች ውድድር 1፡ 05፡34 እና 1፡ 05፡ 16 ሰዓት በመግባት የግማሽ ማራቶን ክብረወሰንን ሁለት ጊዜ ሰብራለች።

  • ዩሊማር ሮጃስ- ቬንዙዌላ

በቤት ውስጥና ከቤት ውጭ በተደረጉ አራት የርዝመት ዝላይ ውድድሮች አሸንፋለች። በቤት ውስጥ በተካሄደ የርዝመት ዝላይ ውድድር 15.43 ሜትር በመዝለል የዓለም ክብረ ወሰን ሰብራለች።

  • ኢሌኔ ቶምፕሰን - ጃማይካ

በሰባት የ100 ሜትር ውድድሮች አሸንፋለች። በዓለም መሪነት 100 ሜትር በ10.85 ሰከንድ ሮጣለች።

ከእነዚህ እጩዎች አሸናፊውን ለመለየት ሦስት የድምፅ አሰጣጥ መንገዶች አሉ። የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት እና የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰቦች ድምፃቸውን በኢሜይል የሚሰጡ ሲሆን አድናቂዎቻቸው ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ድምፅ ይሰጣሉ።

ከአጠቃላይ ድምፁ የምክር ቤቱ ድምፅ 50 በመቶ ይይዛል። የአትሌቲክስ ቤተሰቦችና የሕዝብ ድምፅ ደግሞ እያንዳንዳቸው 25 በመቶ ይይዛሉ።