ኮሮናቫይረስ፡ እስራኤል በኮቪድ-19 ምክንያት ዳግም በሯን ልትዘጋ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
እስራኤል የአይሑድ አዲስ ዓመት ከመግባቱ በፊት እየተስፋፋ ያለውን ኮሮና ለመመከት ጥብቅ እርምጃዎችን ልትወስድ ነው፡፡
ጥብቅ ብሔራዊ ውሸባ እንደሚኖርም ይፋ አድርጋለች፡፡
ከሚቀጥለው አርብ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው አዲስ መመርያ ለሦስት ሳምንታት ይዘልቃል፡፡
ናታንያሁ እርምጃው ‹‹ሁላችንንም ከባድ ዋጋ ያስከፍለናል ነገር ግን ማድረግ አለብን›› ብለዋል፡፡
እስራኤል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀን በአማካይ በቫይረሱ የሚያዙባት ዜጎች ቁጥር 4ሺ በመድረሱ ድንጋጤ ተፈጥሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ላይም ተቃውሞው በርትቶባቸው ቆይቷል፡፡
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ የተቃወሙ የቤቶች ልማት ሚኒስትሩ ያኮቭ ሊዝማን ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቅቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ የተቃወሙት በአይሁድ ትልቅ ክብረ በዓል ዋዜማ ይህ እርምጃ ለምን ይወሰዳል በሚል ነው፡፡
ሰውየው አክራሪ የአይሁድ እምነት ተከታይ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ የአክራሪው ኦርቶዶክስ አይሁድ ፓርቲን የሚመሩትም እርሳቸው ናቸው፡፡
አይሁዳዊያን ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸውን ክብረ በዓላት በተገቢው እንዳናከብር ያደርጋል ብለዋል፣ ያኮቭ ሊዝማን፡፡
ዮም ኪፐር በአይሁድ የቀን አቆጣጠር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምዕመናን ፈጣሪያቸውን ይቅርታ የሚለማመኑበት ቅዱስ ክብረ በዓል ነው፡፡
በሴፕቴምበር 27 ነበር የሚውለው፡፡
እስራኤል እስከአሁን በቫይረሱ የሞቱባት ዜጎቿ ብዛት 1ሺህ 108 ደርሷል፡፡ 153ሺህ ዜጎች ደግሞ ቫይረሱ አጥቅቷቸዋል፡፡
ናታንያሁ ትናንትና እሑድ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የወረርሽኙን መስፋፋት አውስተው ዕለታዊ አማካይ ቁጥር 4ሺ መድረሱ የሚነግረን ነገር አንድ እርምጃ ካልወሰድን ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንደሚሆኑ ነው ብለዋል፡፡
እስራኤል የዜጎችን እንቅስቃሴ ስትገድብ ይህ ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡ መጀመርያ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ከአርብ ጀምሮ በሚተገበረው መመርያ መሰረት ከ10 ሰዎች በላይ ቤት ውስጥ መቀመጥ አይችሉም፡፡
ከ20 ሰዎች በላይ ደጅ መሰብሰብ አይችሉም፡፡
ገበያዎችና ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፡፡
ማንኛውም ዜጋ ለሥራ ወደ መሥሪያ ቤት ካልሆነ ውጭ ከሚኖርበት ስፍራ 500 ሜትር ርቆ መሄድ አይችልም፡፡ ሱፐርማርኬቶችና ፋርማሲዎች ክፍት ሆነው ይቆያሉ፡፡
በቤት ውስጥ ከ10 ሰዎች በላይ መሰብሰብ መከልከሉ፣ እንዲሁም ደጅ 20 ሰዎች በላይ መሰብሰብ አለመቻላቸው ከየትኛውም ህብረተሰብ በላይ የአይሁድ እምነት ተከታዮችን ሕይወት የሚነካ ይሆናል፡፡
በዚህ መመርያ መሰረት አይሁዶች በምኩራባቸው መሰባሰብ አይችሉም፤ ለዘመን መለወጫቸው መዳረሻ እጅግ ቅዱስ ተደርጎ የሚታሰበውን ዮም ኪፐር በዓልን ከቤተሰብ ጋር ማክበርም ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡
ይህ ከአርብ ጀምሮ ተግባር ላይ የሚውለው የሦስት ሳምንታት ብሔራዊ የጤና ወሸባ የእስራኤልን ኢኮኖሚ 2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍለው የፋይናንስ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡














