የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ ቀን ከፍተኛውን የኮቪድ-19 ህሙማን መዘገበ

የሙቀት ልኬት ሲካሄድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ ቀን ቫይረሱ የተገኘባው ሰዎች ከፍተኛውን ቁጥር መመዝገቡን ገለጸ። በ24 ሰዓት ውስጥ 307 ሺህ 930 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

በአንድ ቀን 5 ሺህ 500 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሲሆን፤ ይህም የሟቾችን ቁጥር 917 ሺህ 417 አድርሶታል።

በበሽታው በተያዙ ሰዎች ቁጥር ሕንድ፣ አሜሪካ እና ብራዚል ቀዳሚ ናቸው። በመላው ዓለም 28 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ከነዚህ ገሚሱ የአሜሪካ ነዋሪዎች ናቸው።

ከዚህ ቀደም በአንድ ቀን ከፍተኛ የህሙማን ቁጥር የተመዘገበው ከስምንት ቀን በፊት ሲሆን፤ ቁጥሩም 306,857 እንደነበር ተገልጿል።

በዓለም ጤና ድርጅት አሐዝ መሠረት፤ ትላንት በሕንድ 94,372፣ በአሜሪካ 45,523 እና በብራዚል 43,718 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

በሕንድ እና በአሜሪካ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ሲሞቱ፤ በብራዚል 847 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ሕንድ ነሐሴ ላይ ወደ 2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ሪፖረት አድርጋለች። ይህም ቫይረሱ መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ወር የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው።

በአገሪቱ በአማካይ በአንድ ቀን 64,000 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ። ይህም በሐምሌ ከነበረው 84 በመቶ ጨምሯል። መስከረም ከገባ ወዲህ በየቀኑ የሚሞቱ ሰዎች 1,000 ይጠጋሉ።

በብራዚል ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። ከላቲን አሜሪካ አገሮች ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የታየውም በብራዚል ነው። እስካሁን 131,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በዓለም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች አንድ አራተኛው የሚገኙት በአሜሪካ ነው። እስካሁን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዋል።

ከሐምሌ ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየናረ መጥቷል።

እስካሁን 194,000 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ ከዓለም ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበውም በአሜሪካ ነው።

ሌሎች አገራትስ?

አውሮፓ ውስጥ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው። ቫይረሱ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋትም አለ።

በከፍተኛ ሁኔታ ቫይረሱ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ተጥሏል። ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርጉና አካላዊ ርቀት እንዲጠብቁም ማሳሰቢያ እየተሰጠ ይገኛል።

ቫይረሱ ዳግመኛ ካገረሸባቸው አገሮች መካከል ፔሩ፣ እስራኤል፣ ደቡብ ኮርያ እና አውስትራሊያ ይጠቀሳሉ።

እሁድ በአውስትራሊያዋ ቪክቶሪያ ከተማ ፖሊስ 70 ተቃዋሚዎችን አስሯል። ግለሰቦቹ ከቤት ያለመውጣት ሕግን በመተላለፋቸው ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በሜልቦርን በተካሄደው ተቃውሞ ላይ ቢያንስ ወደ 250 ሰዎች ተሳትፈዋል። ስለ ወረርሽኙ የሴራ ትንታኔዎች ሲስተጋቡም ነበር።

በሌላ በኩል እስራኤል እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ልታደርግ መሆኑ ተገልጿል። የአይሁዳውያን አዲስ ዓመት አርብ ሲከበር፤ እስከ ሦስት ሳምንት የሚቆዩ ጠንካራ የጥንቃቄ እርምጃዎች ይተላለፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በእስራኤል153,000 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ 1,108 መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሐዝ ይጠቁማል።

ኮሮና
Banner