እስያ፡ አዲሱ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሒዳ ሱጋ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዮሺሒዳ ሱጋ ይባላሉ፡፡ ማን ናቸው ደግሞ እሳቸው ካላችሁ ሺንዞ አቤን የሚተኩት ቁልፍ ሰው ናቸው እንላለን፡፡
ዛሬ ሰኞ ሺንዞ አቤን ለመተካት 3 ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል፡፡ አሸናፊው ዮሺሒዳ ሱጋ እንደሚሆኑ ግን ብዙም አጠራጣሪ አልሆነም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ፓርቲያቸው ቀዳሚ እጩ ስላደረጋቸው ነው፡፡የተወለዱት በ1948 እንደነሱ አቆጣጠር ነው፡፡
ቤተሰባቸው እንጆሪ አምራች ገበሬዎች ነበሩ፡፡ ዮሺሒዳ ሱጋ ወደ ፖለቲካ የገቡት ድሮ የፓርላማ አባላት ምርጫን በማስተባበር ሥራ ካገኙ በኋላ ነበር፡፡ ያን ጊዜ እሳቸው ገና ከሆሴይ ከተባለ የግል ዩኒቨርስቲ መመረቃቸው ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ለሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይን በጸሐፊነት አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ወደ ፖለቲካ ጭልጥ ብለው የገቡት፡፡መጀመርያ ለዩኮሓማ ከተማ ተመራጭ ሆነው ቀረቡ፡፡ ይህ 1987 አካባቢ ነበር፡፡
ከዚያ ለጃፓን ምክር ቤት ተመረጡ፡፡ በ2005 ጠቅላይ ሚኒስትር ጁኒቺሮ ኩዊዙሚ የአገር ውስጥ ጉዳይና የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ አድርገው ሾሟቸው፡፡በቀጣይ ዓመት የሚስተር ኮይዙሚ ተተኪ ሺንዞ አቤ ዋና ሚኒስትር አድርገው ሹመት ደረቡላቸው፡፡
እስከ 2007 በዚሁ ቦታ አገልግለዋል፡፡ የሺንዞ አቤና የርሳቸው ግንኙነት እየተጠናከረ ሄዶ ሺንዞ አቤ በ2012 ወደ ሥልጣን ሲመለሱ የካቢኔ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊ አድርገው ቁልፍ ቦታ ሾሟቸው፡፡
ላለፉት 8 ዓመታት ታዲያ ሰውየው የሺንዞ አቤ ቀኝ እጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡በየቀኑ ሁለት ጊዜ ለሚዲያ መግለጫ ይሰጣሉ፤ የጃፓንን ውስብስብ ቢሮክራሲ አብጠርጥሮ በማወቅም ዝናን አትርፈዋል፡፡
ጃፓናውያን የሳቸውን ፊት ያህል የማንንም ፊት በቴሌቪዥን ደጋግመው አይተዋል ማለት ይከብዳል፡፡ሺንዞ አቤ በነሐሴ 28 በጤና ምክንያት ሥልጣን በቃኝ ሲሉ በርካታ ጃፓናዊያን አቤን ማን ሊተካቸው እንደሚችል በትክክል ገምተው ነበር፡፡ ሚስተር ሱጋ፡፡
በመስከረም 2 ሺንዞ አቤ በይፋ ከሥልጣን ለመሰናበት ሲያስታውቁ በጃፓን ታሪክ የካቢኔ ጉዳዮች ጸሐፊነት ቦታ ላይ ረዥም ዘመን በመሥራት የሚታወቁት ሰው ቀጣዩ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ውስጥ ውስጡን መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡
አዲሱ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሚስተር ሱጋ ኮቪድ-19 የበጠበጠውን ግዙፉን የጃፓን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ ይጠበቃል፡፡
የጃፓን ኢኮኖሚ የዓለማችን 3ኛው ግዙፉ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ሚስተር ሱጋ ጃፓን ከአሜሪካ ጋር ያላትን ጥብቅ ግንኙነት አጠናክረው ለመቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ ከቻይናም ጋር ጤናማ ግንኙነትን ይሻሉ፡፡
ሚስተር ሱጋ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመገናኘት መፍቀዳቸው ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡
በ1970ዎቹና 80ዎቹ ሰሜን ኮሪያ አፍና የወሰደቻቸው ጃፓናዊያንን ጉዳይ እልባት መስጠት ፍላጎት አላቸው፡፡
ዮሺሒዳ ሱጋ አሁን 71 ዓመታቸው ነው፡፡












