በሎስ አንጀለስ ሁለት ፖሊሶች ላይ የተኮሰውን ሰው ማንነት የጠቆመ መቶ ሺ ዶላር ይሸለማል

የፎቶው ባለመብት, Reuters / LA Police
በሎስ አንጀለስ ሁለት ፖሊሶች ላይ የተኮሰውን ሰው ማንነት የጠቆመ መቶ ሺ ዶላር እንደሚሸለም ተገለፀ።
አንድ ማንነቱ ለገዜው ያልተለየ ግለሰብ አገር ሰላም ነው ብለው ፖሊስ መኪናቸው ውስጥ ቁጭ ብለው በነበሩ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች ላይ አከታትሎ ከተኮሰባቸው በኋላ ለጊዜው ተሰውሯል፡፡
ይህ የሆነው ባለፈው ቅዳሜ ማታ በሎሳንጀለስ ነው፡፡ ሁለቱም ፖሊሶች እስካሁን ሕይወታቸው ባታልፍም በጽኑ ሕምሙና ክፍል በአደገኛ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት ተብሏል፡፡
የደቂቅ የጎዳና ካሜራ (ሲሲቲቪ) ምሥሎች እንደሚያሳዩት ግለሰቡ ወደ ፖሊሶቹ መኪና ሽጉጥ ደግኖ የተጠጋው በተሳፋሪ ወንበር በኩል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አከታትሎ ተኩሶ ሲሸሽ ይታያል፡፡
ምሥሉ ግን የሰውየውን ማንነት ለመለየት የሚያስችል አልሆነም፡፡የሎስ አንጀለስ የፖሊስ አለቃ አሌክስ ቪላኑቫ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡ የሎስ አንጀለስና አካባቢዋ አስተዳደር ይህንን ወንጀለኛ ያለበትን የሚያውቅ ይጠቁመን እኛ መቶ ሺህ ዶላር ወዲያውኑ እንሸልመዋለን ብሏል፡፡
በአገሬው አቆጣጠር በ2020 ዓ.ም ብቻ 40 ፖሊሶች በሥራ ገበታቸው ላይ ሳሉ ተገድለዋል፡፡
ሁለቱ ፖሊሶች ላይ ጉዳት ቢደርስም በሆስፒታሉ የድንገተኛ ታማሚዎች በር ላይ ጥቂት ሰልፈኞች ፖሊስን የሚያወግዝ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር፡፡ ‹‹የተተኮሰባቸው የፖሊስ መኮንኖች እንዲሞቱ ነው ምኞታችን›› እያሉ ሲቃወሙም ተሰምተዋል፡፡
ለጊዜው ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን አንዷ ግን ጋዜጠኛ ሆና በመገኘቷ ተለቃለች፡፡ ሆኖም ያየችው ሰው እንዳለና እጇ ላይም መረጃ እንደሚገኝ ጠቁማለች፡፡
ጥይት የተተኮሰባቸው ሁለቱ የፖሊስ መኮንኖች ስማቸው ለጊዜው ይፋ ባይሆንም የ31 ዓመት ሴት እና የ24 ዓመት ወጣት ወንድ ፖሊስ እንደሆኑ ግን ተነግሯል፡፡
ከፖሊስ አካዳሚ ከተመረቁና ሥራ ከጀመሩ ገና 14 ወራቸው ነበር፡፡በኅዳር ወር ለመፋለም በምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ያሉት ባይደንና ትራምፕ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡ዶናልድ ትራምፕ ‹‹ይህ አውሬነት ነው›› ሲሉ ባይደን በበኩላቸው ማንኛውም የኃይል ጥቃት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡












