አሜሪካ ፡ ጄኮብ ብሌክ ከሆስፒታል ለጥቁር አሜሪካዊያን መልዕክት አስተላለፈ

ጄኮብ ብሌክ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER

ጄኮብ ብሌክ እያንዳንዷን ደቂቃ በስቃይ እንደሚያሳልፍ ተናገረ።

በ7 ጥይት ተደብድቦ በተአምር የተረፈው ጥቁር አሜሪካዊ ጄኮብ ብሌክ በማያቋርጥ ስቃይ ውስጥ እንደሆነ ከሆስፒታል አልጋው ላይ ሆኖ ተናግሯል።

ጄኮብ በቀጥታ የቪዲዮ ጥሪ ባስተላለፈው መልዕክት ነው ይህን የተናገረው።

ጄኮብ ከወገቡ በታች ያለውን አካሉን ሙሉ በሙሉ ማንቀሳቀስ ተስኖታል። አዲስ ሕይወት የምኖር ይመስለኛል ብሏል ጄኮብ።

የ29 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ፖሊስ በዊስኮንሰን ግዛት ኬኖሻ ከተማ በቅርብ ርቀት ሆኖ 7 ጥይት የተኮሰበት።

ፖሊስ ወጣቱን ላይ ለምን 7 ጥይት እንደተኮሰበትም ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ጄኮብ 7 ጥይቶች ሲተኮሱበት ሦስት ሕጻናት ልጆቹ መኪና ውስጥ ሆነው በቅርበት ክስተቱን እየተመለከቱ ነበር ተብሏል።

ይህ የጄኮብ አሳዛኝ አጋጣሚ በተንቀሳቃሽ ምስል ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።

በተለይም ጄኮብ በሚኖርባት ኬኖሻ ከተማ ተቃውሞው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ሁለት ሰዎች ሞተዋል።

ጄኮብ ባለፈው አርብ ከዚህ አደጋ በፊት የነበረበትን ክስ በቪዲዮ የተከታተለ ሲሆን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ክሱን አስተባብሏል።

ጄኮብ ከሆስፒታል ሆኖ አስተላለፈ የተባለው መልዕክት የተለጠፈው በቤተሰቡ ጠበቃ የትዊተር ሰሌዳ ላይ ነው።

"24 ሰዓት ስቃይ ነው፤ ሌላ ነገር የለም ስቃይ ብቻ። ሌላው ቀርቶ የምተነፍሰው በስቃይ ነው፣ የምተኛው በስቃይ ነው፣ ስገላበጥ ስቃይ ነው፣ ምግብ ስቀምስ ስቃይ ነው" ብሏል ጄኮብ።

"ወደፊት የምራመድባቸውን እግሮቼን ቀሙኝ፤ እንደዋዛ ሕይወቴን ቀሙኝ"

"አብሮነት አይለያችሁ፣ በርትታችሁ ሥሩ፣ ለወገኖቻችን ሕይወትን ቀላል አድርጉላቸው፤ ብዙ መባከን የሌለበትን ጊዜ አባክነናል" ብሏል።

ጄኮብ ሁለት ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ሊያውሉት እየሞከሩ ወደ መኪናው ሲገባ ነው 7 ጥይት ከጀርባው የተተኮሰበት። ጄኮብ በወቅቱ መሳሪያ አልታጠቀም ነበር። ሲተኮስበት ሦስቱ ልጆቹም መኪና ውስጥ ነበሩ።

ኋላ ላይ በተደረገ ምርመራ መኪናው ውስጥ ስለት ተገኝቶበታል።

የጄኮብን በጥይት መመታትን ተከትሎ ኬኖሻ ውስጥ ዝርፊያና ነውጥ የተከሰተ ሲሆን ሁለት ሰዎችም ተገድለዋል። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና እጩው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የጃኮብን ጥቃት ተከትሎ ከተማዋን ጎብኝተዋል።

ባይደን ከጄኮብ ጋር በስልክ የተገናኙ ሲሆን ቤተሰቦቹንም አግኝተዋቸዋል። በእሱ ላይ የተኮሰው ፖሊስም በቁጥጥር ስር እንዲውል ጥሪ አድርገዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ግን የጄኮብን ቤተሰብ አልጎበኙም። የጄኮብ ቤተሰቦችም ትራምፕ እንዲመጡበት እንደማይፈልጉ ተናግረው ነበር።