ጄኮብ ብሌክ የሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ ፍርድ ቤት ቀረበ

ጄኮብ ብሌክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰባት ጊዜ በፖሊስ የተመታው ጄኮብ ብሌክ ከሆስፒታል ሆኖ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ጄኮብ በጥይት ወደ መመታት ለወሰደው ክስተት ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ለፍርድ ቤቱ ቃሉን ሰጥቷል።

በአሁኑ ሰዓት በደረሰበት ጉዳት መንቀሳቀስ የማይችለውና በሆስፒታል አልጋ ላይ የሚገኘው ጄኮብ በቀድሞ የፍቅር ጓደኛው ምስክርነት መሰረት የሰው አጥር ጥሶ በመግባት፣ ጾታዊ ጥቃትና ሕግን አለማክበር በሚሉ ወንጀሎች ክስ ቀርቦበታል።

ከላይ የተጠቀሱት ክሶች የተመሠረቱበት ሐምሌ ወር ላይ ሲሆን ሰባት ጊዜ በጥይት ከተመታበት ጉዳይ ጋር ግንኙነት የለውም።

ለፍርድ ቤቱ በቀረበው ክስ መሰረት ጄኮብ ብሌክ ባሳለፍነው ግንቦት ወር በአንዲት ሴት ላይ ጾታዊ ጥቃት ፈጽሟል። ግለሰቧ ለፖሊስ እንደገለጸችው ጄኮብ የመኪናዋን ቁልፍ እና የባንክ ካርዷን ወስዶ ከአካባቢው ተሰውሯል።

የኬኖሻ ካውንቲ አቃቤ ህግ ቢሮ በበኩሉ ጄኮብ ብሌክ ነሐሴ 23 ላይ በፖሊሶች ቁጥጥር ስር ሊውል ሲል ሰባት ጊዜ ተተኩሶበት ሆስፒታል የገባውም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንደሆነ አስታውቋል።

አርብ ዕለት ጄኮብ ብሌክ ከሆስፒታል አልጋው ላይ ሆኖ በዙም የቪዲደዮ ግንኙነት በኩል ቀርቦ ለፍርድ ቤቱ በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኛ እንዳልሆነ ቃሉን ሰጥቷል።

በወቅቱ የተፈጠረው ምን ነበር?

የዊስኮንሰን ዓቃቤ ሕግ ጆሽ ኩዋል ፖሊሶች በቦታው የተገኙት "የወንድ ጓደኛዬ ያለሁበት ቦታ መምጣት ባይኖርበትም መጥቷል" የሚል ሪፖርት ስለደረሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ሦስት ፖሊሶች ጄኮብን ለማሰር አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመው ነበር። ከዛም ጄኮብ ወደ መኪናው ሲገባ ረስተን ሸስኪ የተባለ ፖሊስ ከጀርባው ሰባት ጊዜ ተኩሶበታል።

ፖሊሶች ከጄኮብ መኪና ስለት እንዳገኙ ገልጸዋል። ጄኮብ ላይ የተኮሰውን የፖሊስ አባል ጨምሮ ሌሎችም ፖሊሶች በጊዜያዊነት ከሥራ ታግደዋል።

የጄኮብ አባት "ልጄ ከሆስፒታል አልጋ ጋር በካቴና ታስሮ ማየት አሳዝኖኛል። የትም መሄድ አይችልም። ታዲያ ለምን በካቴና ያስሩታል" ብለዋል።

የኪኖሻ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ሉተነንት ኤሪክ ክሊንክሽመር፤ ጄኮብ የታሰረው ከዚህ ቀደም የእስር ማዘዣ ወጥቶበት ስለነበረ ነው ብለዋል።

አገረ ገዢው ቶኒ ኤቨርስ ጄኮብ ከሆስፒታል አልጋ ጋር በካቴና መታሰሩ አያሳስብዎትም ተብለው ሲጠየቁ፤ "ማሰር ለምን እንዳስፈለገ አይገባኝም። ሰባት ጊዜ ከጀርባው የተተኮሰበት ሰው ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ ሲቪል ሊበርቲስ ዩኒየን የኪኖሻ ግዛት የፖሊስ ኃላፊ ከሥራ እንዲነሱ ጠይቋል። ኃላፊው "የነጭ የበላይነትን የሚደግፉ" እና "የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ ሰዎችን የኮነኑ ናቸው" ተብለዋል።

የከተማው ከንቲባ ግን የፖሊስ ኃላፊው እንደማይነሱ ተናግረዋል።