የህፃናት ጥቃት፡ የናይጄሪያ ፍርድ ቤት የ12 ዓመቷን ታዳጊ የደፈረውን ግለሰብ ሞት ፈረደበት

መደፈርን የሚቃወሙ የተቃውሞ ሰልፎች

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

በናይጄሪያዋ ካኖ ግዛት የአስራ ሁለት ዓመቷን ታዳጊ የደፈረው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ እስላማዊው ፍርድ ቤት በይኖበታል።

የካኖ ግዛት የፍትህ ቢሮ ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የላይኛው ሻሪያ ፍርድ ቤት የ61 ዓመቱን ግለሰብ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።

ታዳጊዋንም ከከተማ ወጣ ባለ ፋርሳ በተባለ የገጠር መንደር ውስጥ በሚገኝ ገላጣ ስፍራ ከዓመት በፊት ግለሰቡ ደፍሯታል ተብሏል።

በደፋሪዎች ላይ ያልተለመደ በተባለው በዚህ ብያኔም መሰረት የእስልምና ሕግጋትን ተከትሎ ግለሰቡ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ነው ተፈረደበት። ግለሰቡ ባለ ትዳር እንደሆነም ተገልጿል።

ደፋሪው ይግባኝ የመጠየቅ ሰላሳ ቀናት ጊዜ አለው። በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በናይጄሪያ የሚደፈሩ ህፃናትና ሴቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ ነበር።

በዚህ ሳምንት ውስጥ በካኖ ከተማ የእስልምና ፍርድ ቤቶች የሞት ቅጣት ሲፈርዱ ሁለተኛቸው ነው።

ሰኞ ዕለትም አንድ ዘፋኝ የነብዩ መሐመድን ስም በግጥሞቹ አንቋሻል በሚልም የሞት ፍርድ ተበይኖበታል።

በሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ የሸሪያ ሕግ ተግባራዊ ካደረጉ በርካታ ግዛቶች መካከል ካኖ አንዷ ናት።

በባለፉት ሁለት አስርት ዓመታትም ከሌሎች አገሪቷ ሕጎች ጋር ሆኖም እጅ ለእጅ ሆኖ ይሄዳል።

ምንም እንኳን በርካታ ሰዎች የሞት ፍርድ ቢፈረድባቸውም እስካሁን ተግባራዊ የሆነው አንድ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።