ሪፐብሊካኖች ለኮቪድ ማገገምያ አንድ ትሪሊዮን ዶላር መደቡ

ዶናልድ ትራምፕና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሪፐብሊካኖች ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ክፉኛ የተሸመደመደውን ምጣኔ ሀብት ለማነቃቃት አንድ ትሪሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

እቅዱ ካካተታቸው መሀል መቶ ቢሊዮን ዶላሩ ለትምህርት ቤቶች ድጎማ፣ እንዲሁም ለብዙ አሜሪካዊያን 1,200 ዶላር ክፍያ መስጠትን ይጨምራል፡፡

ይህ እቅድ ተግባራዊ ከሆነ ለሥራ አጦች ይከፈል የነበረውን 600 ዶላር ይተካል ተብሏል፡፡

ይህ የገንዘብ መጠን ገና ከዲሞክራቶች ጋር ክርክር ከተደረገበት በኋላ የሚጸድቅ ሲሆን ዲሞክራቶች ግን እቅዱን ገና ከወዲሁ እየተቹት ነው፡፡ 'አንድ ትሪሊዮን ዶላር ምን አላት'፣ ሲሉ የገንዘቡን መጠን ማነስ አብጠልጥለዋል ዲሞክራቶች፡፡

አሜሪካ እስከዛሬ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ እስካሁን 2.4 ትሪሊዮን ዶላር ማገገምያ ገንዘብ አውጥታለች፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የዋለው አሜሪካዊያን ቤተሰቦችን ለመደጎምና ቢዝነሶችን ለማነቃቃት ነበር፡፡ የምጣኔ ሀብት ተንታኞች ግን ገንዘቡ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም እያሉ ነው፡፡

ይህ አዲሱ የሪፐብሊካን ምክረ ሐሳብ ለሥራ አጥ አሜሪካዊያን ይሰጥ የነበረውን ሳምንታዊ የ600 ዶላር ድጎማ ወደ 200 ዶላር ዝቅ የሚያደርግ ሲሆን ይህ ግን የሚቆየው ሌላ ውጤታማና የዜጎችን 70 ከመቶ ገቢ የሚደጉም አዲስ መርሀግብር እስኪጀመር ብቻ ነው፡፡

አዲሱ ምክረ ሐሳብ ለሥራ አጥ አሜሪካዊያን ይሰጥ የነበረውን የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ያለመው በርካታ ዜጎች በድጎማው የሚያገኙት የገንዘብ መጠን ሥራ ሠርተው ከሚያገኙት የተሻለ ስለሆነ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዳይመለሱ አድርጓቸዋል በሚል ነው፡፡

ሴናተር ሚች መክኔል ‹ሪፐብሊካኖች በዚህ ሳምንት ቀነ ገደቡ የሚያበቃውን የሥራ አጥ ዜጎችን የገንዘብ ድጎማ ማርሀ ግብር መቀጠል ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ይህን ስናደርግ ሕዝቡ ወደ ሥራ እንዲመለስ በሚያበረታታ መልኩ መሆን እንዳለበት አምነናል› ብለዋል፡፡

በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የዲሞክራቶች ተጠሪ ሴናተር ሹመር የሪፐብሊካኑን ምክረ ሐሳብ፣ ‹በጣም የዘገየና በጣም ትንሽ› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

አሜሪካ ካለፈው የካቲት ጀምሮ 15 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ አጥ ሆነውባታል፡፡ በዚህም የተነሳ ከአምስት አሜሪካዊያን አንዱ የሥራ አጥነት ድጎማ ገንዘብ እየወሰደ ይገኛል፡፡

‹ይህ እጅግ አደገኛ ቀውስ ነው፤ ጊዜ እየቀደመን ነው፤ እርምጃ መውሰድ አለብን› ብለዋል ሴናተር ሹመር፡፡

‹የሪፐብሊካኑ አዲስ እቅድ ዜጎች ያገኙት የነበረውን ድጎማ በ30 እጅ የሚቀንስ ነው፤ በዚህ ዜጎች ወደ ሥራ ለመመለስ በማይችሉበት ሁኔታ ድጎማን መቀነስ ስሜት አይሰጥም› ብለዋል፡፡

ዲሞክራቶች በበኩላቸው ያቀረቡት ምክረ ሐሳብ አሜሪካ 3 ትሪሊዮን ዶላር የኮቪድ ማገገምያ ገንዘብ እንድታዘጋጅ ይጠይቃል፡፡ ይህም ገንዘብ በዋናነት የግዛት አስተዳደሮችን ለመደጎም የሚውል ነው፡፡ የአሜሪካ ብዙ ግዛቶች በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት የበጀት ቀውስ ገጥሟቸዋል፡፡

ኮሮና
Banner