ኮሮናቫይረስ፡ ፈተና ውስጥ የገባው የሕንድ ሻይ ቸርቻሪዎች ሕይወት

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት በሕንዷ ኒውደልሂ ከሰዓት አካባቢ በርካታ የቢሮ ሠራተኞች ከየሚሰሩባቸው መስሪያ ቤቶች በመውጣት በአቅራቢያ ወደሚገኙ ሻይ መሸጫዎች ይጎርፋሉ።
ሻያቸውን የሚጠብቁ ሰዎች በየመንገዱ ተሰልፈው መመለክትም የተለመደ ነገር ነበር።
ከሥራ ባልደረቦች ጋር ወደ መንገዶች ወጣ ብሎ በወተትና በቅመም የተፈላ ሻይ እየተጎነጩ የእረፍት ጊዜን ማሳለፍ እንደ ባህል የሚቆጠርም ጭምር ነው።
ሰብሰብ ብለው ስለአለቆቻች የሚያማርሩበትና የግል ሕይወታቸውን የሚጨዋወቱበት ልዩ አጋጣሚም ነው።
ነገር ግን ልክ መጋቢት 16 ላይ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተሰራጨ የነበረውን ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በማሰብ ሕንድ ለሦስት ወራት የሚቆይ አጠቃላይ የእንቅስቃሴ ገደብ አስተላለፈች።
በዚህ ምክንያት ሁሉም መስሪያ ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ በየቦታው ሻይና የተጠበሰ ድንች የሚሸጡት ቸርቻሪዎች ብቻቸውን ቀርተዋል። በመጨረሻም እነሱም ሱቃቸውን ለመዝጋት ተገደዋል።
አሁን ገደቦቹ ቀስ በቀስ እየላሉ መምጣታቸወውን ተከትሎ አንዳንድ ሻይ ቸርቻሪዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው እየተመለሱ ይመስላል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን በርካታ የቢሮ ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው እየሰሩ መሆኑን ተከትሎ የደንበኞቻቸው ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።
ሌላው ቀርቶ ወደ መስሪያ ቤታቸው ተመልሰው ለመስራት የተገደዱት እንኳን ሰዎች በሚሰበሰቡበት አካባቢ መገኘትና አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ ክልክል በመሆኑ ነገሮችን ከባድ አድርጎባቸዋል።
ሕንዳውያን ለሻይ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ሕንድ በዓለማችን ከቻይና በመቀጠል ሁለተኛዋ ከፍተኛ ሻይ አምራች አገር ስትሆን ከምታመርተው ሻይ 80 በመቶ የሚሆነው እዚያው አገር ውስጥ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው።
ከሕንድ ሕዝብ 88 በመቶ የሚሆነው ሰው ሻይ ይጠጣል። ሕንድ ውስጥ በማንኛውም ሰዓትና በማንኛውም ሁኔታ ሻይ ይጠጣል።
አርጁን ኪሾሬ በአንድ የጤና ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያ ሆኖ ይስራል። ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት በቀን ቢያንስ አምስት ጊዜ ሻይ ለመጠጣት ወደ ሻይ ቸርቻሪዎቹ ይሄድ እንደነበር ያስታውሳል።
ከሰዎች ጋር ተጋፍቶ ሻይ መጠጣትም ከዕለት ተዕለት ተግባሩ መካከል አንዱ ነበር።
“አሁን ወደምሰራበት ድርጅት የመጣሁት ከጥቂት ወራት በፊት ነበር። ስለዚህ አዳዲስ ሰዎችን ለመተዋወቅና የሥራ ባልደረቦቼን በደንብ ለማወቅ የሻይ ሰዓት በጣም ወሳኝ ነው’’ ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አሩል ካኒ እንደሚለው ሕንዳውያን ስለ ጠባብ ቦታዎችና አካላዊ ርቀት ከሌላው ዓለም የተለየ አስተሳሰብ ነው ያላቸው።
‘’የመንግሥት ሠራተኛውም ሆነ የግል ተቀጣሪ፤ ተማሪዎችም ሆኑ ነጋዴዎች እንደ ትልቅ የእረፍት ጊዜ የሚቆጥሩት ይህንን የሻይ ሰዓት ነው። በተጣበበና በተጨናነቀ መልኩ መሆኑ ደግሞ ማንንም አያሳስብም ነበር።‘’
ሕንድ ውስጥ በአለቃና በበታች ሠራተኞች መካከል ከፍተኛ የሆነ መራራቅ አለ። በዚህም ምክንያት ሠራተኞች የሚሰማቸውንና ማለት የሚፈልጉትን ነገር በግልጽ ከአለቆቻቸው ጋር መነጋገር አይችሉም።
ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ከመሰል ባልደረቦቻቸው ጋር ስሜታቸውን መጋራት ነው። እነዚህ ሻይ መሸጫዎች ደግሞ ይሀንን ለማድረግ ትክክለኛ ቦታዎች ናቸው።
የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በርካታ የመንገድ ላይ ቸርቻሪዎችን ሕይወት አመሰቃቅሏል። ኢኮኖሚውንም ቢሆን ቀላል በማይባል መልኩ አድቅቆታል።
ነገር ግን ይህ የዕለት ተዕለት የኑሮ መስተጓጎል ያስቀረው ሻዩን ብቻ አይደለም።
ልክ አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ ባስመጠች የመጀመሪያዎቹ ቀናት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንገድ ላይ ቸርቻሪዎች፣ የጉልበት ሠራተኞችና ተመላላሽ የቤት ሠራተኞች መሄጃ ጠፍቷችው ታይተዋል።
አብዛኞቹም ወደመጡባቸው የገጠር ከተሞች ሲመለሱ ተስተውለዋል። መመለሻ ገንዘብ የሌላቸው ደግሞ በየመንገዱ ተሰብስበው መንግሥት እርዳታ እንዲያደርግላቸው ሲማጸኑ ነበር።
ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው ለመጓዝ የተገደዱም አልጠፉም።
በምዕራባዊ ዴልሂ ሻይ የሚቸረችረው ፓቫን ኩማር እንደሚለው ለሰዓታት ረጅም ሰልፍ ያስተናግድ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በቀን እጅግ በጣም ትንሽ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው የሚመጡት።
ከሚመጡት ደንበኞች መካከል አብዛኞቹ ደግሞ ሹፌሮች ሲሆኑ እነሱም ሙሉውን የሻይ ዋጋ እንኳን መክፈል የማይችሉ ናቸው።
የሕንድ ብሔራዊ የመንገድ ላይ ቸርቻሪዎች ማኅበር በበኩሉ አባላቱን ለመደጎም በማሰብ እስከ 132 ዶላር የሚደርስ ብድር ማመቻቸቱን አስታውቋል።
ምንም እንኳን የመንገድ ላይ ሻይ ቸርቻሪዎች በሕንድ የቢሮ ሠራተኞች ሕይወት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራቸው የሚመለሱ አይመስልም።














