ኮሮናቫይረስ: “ለሴቶች ተብለው የተሠሩ የሀኪም መገልገያዎች እንፈልጋለን”

ከሦስት ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት አብዛኞቹ በአውሮፓና በአሜሪካ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሀኪሞች መገልገያዎች ወንድን ታሳቢ አድርገው እንደሚመረቱ ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, Dr Arghavan Salles

የምስሉ መግለጫ, ከሦስት ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት አብዛኞቹ በአውሮፓና በአሜሪካ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሀኪሞች መገልገያዎች ወንድን ታሳቢ አድርገው እንደሚመረቱ ያሳያል

የህክምና ባለሙያዎች የሚጠቀሙባቸው እንደ ጓንት፣ ገዋን፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያለ መሣሪያ (ፐርሰናል ፕሮቴክቲቭ ኢክዊፕመንት ወይም ፒፒኢ) ለሴቶች እንዲሆን ተደርጎ የማይሠራበት ጊዜ አለ የሚል ቅሬታ እየተሰማ ነው።

እነዚህ ቁሳ ቁሶች ሀኪሞች ራሳቸውን ከኮቪድ-19 እንዲከላከሉ ይረዳሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ክፍል በበኩሉ መሣሪያዎቹ ለወንዶችም ለሴቶችም ምቹ በሆነ መንገድ ነው የሚሠሩት ብለዋል። ሆኖም ግን የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በስፋት አነስተኛ የሚባሉትን የሀኪም መገልገያዎች ሳይቀር ሴቶች ሊጠቀሙባቸው አልቻሉም።

በዩኬ 77 በመቶ የሚሆኑት የህክምና ባለሙያዎች ሴቶች ናቸው። ሀኪሞች ራሳቸውን ለመከላከል የሚጠቀሙባቸው ቁሳ ቁሶች ከሚፈለገው ስፋት በላይ ሲኖራቸው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አይችሉም።

የአገሪቱ የጤና ክፍል ባወጣው መግለጫ እነዚህ መገልገያዎች ሴቶችም ወንዶችም እንዲጠቀሙባቸው ታስበው ስለተዘጋጁ በተለያየ መጠን ይገኛሉ ብሏል።

የሮያል ኮሌጅ ኦፍ ነርሲንግ በበኩሉ፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ለነርሶች ምቹ አይደሉም ብለዋል። አንዳንድ ሴት ሀኪሞች ፎቷቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ፤ መገልገያዎቹ ምቹ እንዳልሆኑ ሲናገሩ ነበር።

የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲዋ ዶ/ር አርጋቫን ሴልስ “ኤን-95 ማስኮች ያሉት በሁለት መጠን ብቻ መሆኑ ያስገርማል” ይላሉ። ሌሎች መገልገያዎች ያለ አማራጭ፣ በሁለት መጠን ብቻ እንደማይቀርቡም ይናገራሉ።

አንዲት የሥራ ባልደረባቸው ለሷ ፊት የሚሆን ጭንብል ስላላገኘች ወደ ቤት የተመለሰችበት ቀን እንደነበርም ያስታውሳሉ።

አነስተኛ የሚባሉት ጓንቶችና መነጽሮችም ከመጠን በላይ ትልቅ እንደሆኑ በመጥቀስ “እጄ 6 ኢንች ቢሆንም 6.5 ኢንች ጓንት ነው የማደርገው” ይላሉ።

‘ኢንቪዝብል ውሜን’ ወይም የማይታዩ ሴቶች የተሰኘ መጽሐፍ ያሳተመችው ካሮላይን ክሪዶፔሬዝ፤ አብዛኞቹ የሀኪም መገልገያዎች ወንዶችን ታሳቢ በማድረግ ነው የተሠሩት ትላለች።

“ትንሽ ሲባል ለወንድ የሚሆን በትንሽ መጠን የተሠራ ለማለት እንጂ ለሴት የሚሆን ትንሽ መጠን ያለው መገልገያ አይደለም” ስትል ታስረዳለች።

የህክምና ባለሙያዎች ባጠቃላይ መገልገያ ለማግኘት በተቸገሩበት በዚህ ወቅት ሴት ሀኪሞች ደግሞ ተጨማሪ ፈተና ገጥሟቸዋል። የሴቶች እኩልነት ፓርቲ ነገሩ “እጅግ አሳፋሪ ነው” ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

ከሦስት ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት አብዛኞቹ በአውሮፓና በአሜሪካ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሀኪሞች መገልገያዎች ወንድን ታሳቢ አድርገው እንደሚመረቱ ያሳያል።

ኮሮና