ኮሮናቫይረስ፡ በአማራ ክልል “ህጋዊ አሰራርን ያልተከተሉ” 7ሺህ የሚሆኑ ንግድ ቤቶች ታሸጉ

የኮሮናወረርሽኝን ተከትሎ በአማራ ክልል በህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ 194 ነጋዴዎች ታስረው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ተጠቆመ።
"ከወረርሽኙ መከሰት በኋላ ህገወጥ የንግድ ሥራ የሚሠሩ ነጋዴዎች" አሉ ያሉት የአማራ ክልል የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በህገወጥ ንግድ ከመሳተፍ "ጊዜው ችግር የምንካፈልበት ነው" ብለዋል።
ነጋዴዎች ህጋዊ አሰራርን እንዲከተሉ ትምህርት ሲሰጥ እንደቆየ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከማስተማር ባሻገር ከማስጠንቀቂያ መስጠት እስከ ድርጅት ማሸግ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በክልሉ "49ሺህ በላይ ድርጅቶች ተፈትሽፈዋል። ወደ 21 ሺህ የሚደርሱት ችግር ተግኝቶባቸዋል። 7 ሺህ የሚሆኑት የታሸጉ ሲሆን 194 ግለሰቦች ታስረው ምርመራ እየተካሄደ ነው" በውለዋል።
ቢሮው ከህገወጥ ንግድ በተጨማሪ በሽታውን ለመከላከልም እየሠራ መሆኑን አቶ ተዋቸው አስታውቀዋል።
እንደኃላፊው ገለጻ ከሆነ በገበያ ቦታዎች ያሉትን ጥግግቶችን ለመቀነስ ከነበሩት የገበያ ቦታዎች በተጨማሪ አዳዲስ የገበያ ቦታዎችን በማስጀመር፤ በንግድ ሱቆች ውስጥ ገዢና ሻጭ ርቀታቸው እንዲጠብቁ በማድረግ እና የቤት ለቤት የሽያጭ አገልግሎትን በማስፋፋት ሰዎች ከቤታቸው አስገዳጅ ካልሆነ በቀር እንዳይወጡ ለማደረግ ቢሮው እየሰራ ነው።
ቢሮው ወደ ገበያ ቦታዎች የሚሄዱ ሰዎችም የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርጉ፤ በገበያ ቦታዎች ርቅተን እንዲጠብቁ፤ በገበያ ቦታዎች የንጽህና መጠበቂያዎችን እንዲጠቀሙ እና ገበያ ደርሰው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ሰዎች ከመግባታቸው በፊት እንዲታጠቡ ትምህርት እየሰጠ መሆኑም ተገልጿል።
በገበያ ቦታዎች የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አስገዳጅ ነው ወይ? ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ""እንደምክረ ሃሳብ ነው የቀረበው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርጉ አይልም። ገበያው ላይ ያለው ጥግግት በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል። የገበያ ቦታዎች ጥግግቱ ከሁለት ሜትር የሚያንስበት አጋጣሚ ይበዛል። ከርቀት መጠበቅ ሌላ የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ደግሞ የትንፋሽ ለትንፋሽ ልውውጥን ያስቀራል። በሽያጭ መካከል ያለው ቅርርብ ትንሽ በመሆኑ ነው አስገዳጅ ሳይሆን ምክረ ሃሳብ ነው ያቀረብነው" ሲሉ መልሰዋል።
አዋጁ ሃገራዊ በመሆኑ ክልሉ ሌላ አዋጅ አያወጣም ያሉት ምክትል ቢሮ ኃፊው "በአዋጁ ገበያ የሚወጣ የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አለበት አይልም፤ በደንቡም አልተካተተም። ስለዚህ ከማስገደድ በማስተማር የተሻለ በመሆኑ ምክረ ሃሳብ እናቀርባለን። የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ባለማድረግ እርምጃ አንወስድም ግን ከበሽታ እንደሚከላከል እያስተማርን ነው" ብለዋል።
የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አቅርቦት ችግር መኖሩንም አቶ ተዋቸው ጠቁመው "ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ድርጅቶች እየሠሩ ነው። ህብረተሰቡ ትምህርቱን ተቀብሎ የአፍና እፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እፈልጋለሁ እንኳን ቢል ምርቱ ላይም በደንብ እየሰራን ነው" ብለዋል።















