የኢንስታግራም ተጽዕኖ ፈጣሪው 400 ሚሊየን ዶላር በማጭበርበር ወንጀል ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, DUBAI MEDIA OFFICE/TWITTER
'ሃሽፓፒ' በሚል ስም የሚታወቀው ናይጄሪያዊው የኢንስታግራም ዝነኛ ሰው ራይመንድ ሊግባሎዲይ፤ 435 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በማጭበርበር ወንጀል መታሰሩን የዱባይ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ፖሊስ 'ፎክስ ሃንት 2' ሲል በጠራው ልዩ የወንጀል ምርመራ ዱባይ ውስጥ በተመሳሳይ የማጭበርበር ወንጀል ሌሎች 12 ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡
በዚህ የማጭበርበር ወንጀል በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ 2 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ተጠቂዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ነዋሪነቱን ዱባይ ያደረገው ናይጄሪያዊ የማህበራዊ ሚዲያው ሰው፤ 'ሃሽፓፒ' የተሳካለት የንግድ ሰው እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት ይናገራል፡፡
በሌላ በኩል የአገሪቷ ባለሥልጣናት እስሩን ለመፈጸም ያደረጋቸውንና አራት ወራት የፈጀውን የወንጀል ምርመራ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚድያ ገጻቸው አጋርተዋል፡፡
ቪድዮው 'ሃሽፓፒ' እና አጋሮቹ ሆቴላቸው እንዳሉ ፖሊስ ሰብሮ ሲገባ እና በቁጥጥር ሥር ሲያውላቸው ያሳያል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ፖሊስ፤ 'ሃሽፓፒ' በሐሰተኛ ደረሰኞች የገንዘብ ማጭበርበር፣ የሳይበር ማጭበርበር፣ የመረጃ ምንተፋ፣ የባንክ ማጭበርበር፣ ሃሰተኛ ማንነት በመጠቀም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውጭ ወንጀሉን ይሰራበት የነበረውን ድብቅ የኦንላይን ኔትወርክ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡
ቡድኑ የድርጅቶችን ኢሜል በመጥለፍ እንዲሁም ድረ ገጾችን በመቅዳት ገንዘቦች ወደ ራሱ የባንክ ሒሳብ ቁጥር እንዲገባ በማድረግም ተወንጅሏል፡፡
የዱባይ ፖሊስ መቼ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ያለው ነገር የለም፡፡













