ጉግል ዜና ለሚያሰራጩ ሚዲያዎች ገንዘብ መክፈል ሊጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጉግል በሦስት አገራት ውስጥ ጥሩ ለሚባሉ ዘገባዎች ክፍያ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ገለጸ።
የኢንተርኔት መምጣትና የመረጃ ሱናሚ የዜና ኩባንያዎችን በነዋይ ረገድ አንኮታኩቷቸዋል። ጋዜጠኞችና በጋዜጦች የሚጻፉ መረጃዎች በቀላሉ በኢንተርኔት ስለሚለቀቁ ሰዎች ጋዜጣና መጽሔት መግዛት ፋይዳው እየጠፋባቸው ነው።
ጉግልና ፌስቡክ የጋዜጠኞችን ልፋት መና እያስቀሩ ነው በሚል ለዘመናት ሲተቹ ነበር።
ጉግል ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ለአንዳንድ "ደረጃቸውን ለጠበቁ" ዘገባዎች ክፍያ እጀምራለሁ ማለቱ ተሰምቷል።
ጉግል ደንበኞቹ አንዳንድ "ከፍ ያለ ጥራት ያላቸውን ዘገባዎች" እንዲያነቡ ለማበረታት ሲል የዘገባዎቹን ላዘጋጀው ፕሬስ የተወሰነ ክፍያ ሊከፍል ተስማምቷል።
ይህንን አዲስ የነዋይ ሽርክና ከሚጀመርባቸው ፕሬሶች መሀል የአውስትራሊያ፣ የብራዚልና የጀርመን ግዙፍ መገናኛ ብዙሃን ይገኙበታል።
ብዙዎቹ የበይነመረብ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በጋዜጠኞች የተለፉባቸውን ዘገባዎች በነጻ ለተጠቃሚዎች ስለሚያቀርቡ ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳባቸው ቆይቷል።
ይህ የጉግል ውሳኔ ከመሰማቱ ቀደም ብሎ አውስትራሊያ፣ ጉግልና ፌስቡክ ለዜና ዘጋቢዎች ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚያስገደድ ደንብ ተግባር ላይ ለማዋል እያጤነች ነበር።
ፈረንሳይ በበኩሏ ጉግል ለዜና አሳታሚዎች ተገቢውን ክፍያ እንዲከፍል ቀደም ብላ መመሪያ አውጥታለች።
ለረዥም ጊዜ በበይነመረብ የሚሰራጩና የተደከበማቸው ዘገባዎችን ከኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ጋር የተዛመዱ ኩባንያዎች ለደንበኞቻቸው በነጻ መመገባቸው አግባብ ነው ወይ በሚለው ዙርያ ክርክር ሲደረግ ነበር።
አንድ የኢንተርኔት ተገልጋይ ሰው ቁልፍ ቃል ተጠቅሞ መረጃ ሲፈልግ በቅድሚያ የሚያገኛቸው ዘገባዎችን በትንሽ መጠንም ቢሆን ካነበባቸው ጉግል ለዚያ ዘገባ አሳታሚ ወይም ጋዜጠኛ መክፈል ይኖርበታል የሚሉ አሉ።
ሌሎች ደግሞ ደንበኛው ዜናው የተጻፈበትን ድረገጽ ከፍቶ ሙሉ ዘገባ ሲያገኝ ነው ክፍያው መፈጸም ያለበት በሚለው ዙርያም ሰፊ ክርክሮች ተደርገዋል።
ጉግል ከዚህ በኋላ ከፍተኛ ጥራት ላላቸው የዜና ዘገባዎች ክፍያን ይፈጽማል ይላል በድርጅቱ የጡመራ ሰሌዳ ላይ የተነበበው መረጃ። ሆኖም ጉግል "ከፍተኛ ጥራት ያላቸው" ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አልተብራራም።
ጉግል ከዚህ በተጨማሪ ለዜና ዘገባቸው ክፍያ የሚጠይቁ ድረ ገጾችን ደንበኞቹ በነጻ እንዲያገኟቸው ለማስቻል ከዜና አሳታሚዎች ጋር ውል እንደሚገባ ይጠበቃል።
ይህ እድል ዜና አቅራቢዎች አዳዲስ ደንበኞችን እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ አዲስ የገቢ ምንጭ ይሆንላቸዋል የሚል ተስፋ አለ።
ሩፐርት መርዶክና የጀርመኑ አክሴል ስፕሪንገርን የመሰሉ ግዙፍ የዜና አታሚ ድርጅቶች እነ ጉግልን በእኛ ላብ እየበላችሁ ነው ሲሉ ይከሷቸዋል።
ጉግል ዛሬ ያሳለፈው ውሳኔ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ተጠብቋል።
ጋዜጠኝነትን በብዙ ድካም የሚሰሩ አገር በቀል ሚዲያዎች በዚህ የጉግል የክፍያ ሥርዓት ይካተቱ አይካተቱ በዝርዝር የተባለ ነገር የለም።
ክፍያው በየትኞቹ ቋንቋዎች ለሚዘጋጁ የዜና ዘገባዎች እንደሚሆንም አልተብራራም።
ተቺዎች "ከፍተኛ ጥራት ያላቸው" የሚለውን የጉግል ደንብ ሳንሱር ሲሉ እየተቹት ነው። እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ሰዎች ምን ማንበብና ምን አለማንበብ እንዳለባቸው ሊወስኑ መብት የላቸውም ይላሉ የሚዲያ አዋቂዎች።
በዚህ የክፍያ ሥርዓት ለመግባት ቅድሚያውን የያዙት ዜና አታሚዎች የጀርመኑ ሰፒገል ግሩፕ፣ የአውስትራሊያው ኢንክዊንስላንድና ኢንዴይሊ እንዲሁም የብራዚሉ ዳያሪዮስ ናቸው።












