በርካቶች ኮሮናቫይረስን ለማከም በሚደረገው ሙከራ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆኑ

ፕላዝማ

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ከኮሮናቫይረስ የዳኑ ሰዎች የደም ፕላዝማ ሆስፒታል የገቡ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን ለማከም ያስችል እንደሆነ ለማወቅ በሚደረገው ሙከራ ላይ ፈቃደኛ ሆኑ።

ከ6,500 በላይ ሰዎች በሙከራው ላይ ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሲሆን ሙከራውም መካሄድ ጀምሯል። በዚህም ከበሽታው ካገገሙ ሰዎች ደም ውስጥ በሚወሰደው የተፈጥሮ መከላከያ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማዳን ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ባለፈው ሳምንት የብሪታኒያ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ከኮሮናቫይረስ ካገገሙ ሰዎች ደም ማሰባሰብ ጀምሯል። እንግሊዝ ውስጥ 148 ሰዎች እስካሁን ደማቸውን ለዚሁ አላማ መለገሳቸው ተገልጿል።

ባለሙያዎች ተጨማሪ የደም ለጋሾችን ለማግኘት ቀደም ሲል ቫይረሱ ተገኝቶባቸው የነበሩ ሰዎችን ለማግኘት መረጃ በመፈተሽ ስልክ ደውለው ፈቃደኛ መሆናቸውን ይጠይቃሉ ተብሏል።

አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ሲያዝ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ ሥርዓቱ በሽታን አምጪ ተህዋስን የመከላከያ ዘዴን ያዘጋጃል፤ ይህም ቫይረሱን በማጥቃት ወደ በሽታ እንዳይሸጋገር ያደርጋል።

ይህ ሂደትም በአንድ ወር ውስጥ የሚፈጠር ሲሆን ፕላዝማ በተባለውና በደም ውስጥ ባለው ፈሳሽ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ነው።

ይህንን ፕላዝማ በኮቪድ-19 በጠና ለታመሙ ሰዎች በመስጠት ከቫይረሱ ጋር ፍልሚያ የገጠመውን የእራሳቸውን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ ሥርዓት በማጠናከር ከበሽታው እንዲያገግሙ ለማገዝ ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

በአራት የዩናይትድ ኪንግደም ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚካሄደውን ይህንን ሙከራ የሚመሩት ዶክተር ማኑ ሻንካር፤ የኮቪድ-19 ቫይረስ አዲስ በመሆኑ ምክንያት ብዙም የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ጨምረውም "ማናችንም በተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ ሥርዓትችን ውስጥ ከዚህ ቫይረስ ሊከላከለን የሚችል ዘዴ የለንም" በማለት አሁን የሚደረገውን ሙከራ አስፈላጊነት አመልክተዋል።

ኮሮና
Banner