ኮሮናቫይረስ፡ እስካሁን የኮሮናቫይረስ ያልደረሰባቸው አገራት እነማን ናቸው?

በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ ያለችው የቱቫሉ ደሴት አንድ ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ ያለችው የቱቫሉ ደሴት አንድ ክፍል

የዛሬ ሦስት ወር አካባቢ ኮሮናቫይረስ የሚባል ነገር በቻይና ተገኘ ተባለ። አንድም ሰው ከቻይና ውጭ አልተያዘም ነበር ያኔ።

ከጃንዋሪ 13 ወዲህ ከቻይና ውጭም አለ ተባለ። መጀመርያ በታይላንድ፣ ከዚያም በደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በአሜሪካ ተገኘ ተባለ።

አሁን አንድ ሚሊዮን ሰዎች በዓለም ዙርያ በወረርሽኙ ተይዘዋል።

ከኔፓል እስከ ኒካራጓ፣ ከኢኳዶር እስከ ኢትዮጵያ በሽታው ያልገባበት የለም ማለት ይቻላል፡። የሆስፒታል አልጋዎች ሞልተዋል፤ አገሮች ለደቂቃ አስበውት የማያውቁት የፊት ጭምብል እንኳ አንሷቸዋል።

የምር ግን ኮሮናቫይረስ ያልገባበት አገር ይኖር ይሆን?

በሚገርም ሁኔታ መልሱ "አዎ" ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት 193 ናቸው። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ 19 አገራት ኮሮናቫይረስ የሚባል ነገር በአገራችን አይተንም ሰምተንም አናውቅም ይላሉ።

እነዚህን አገራት መዘርዘር ይቻላል። ብዙዎቹ ስማቸው ለጆሮም ለአይንም እንግዳ ነው።

ኮሞሮስ፣ ኪሪባቲ፣ ሌሶቶ፣ የማርሻል ደሴቶች፣ ሜክሮኒሺያ፣ ናዉሩ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፓላዉ፣ ሳሞዋ፣ ሳዎ ቶሜና ፕሪንሲፔ፣ ሶሎሞን ደሴቶች፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታጃኪስታን፣ ቶንጋ፣ ቱርክሜኒስታን፣ ቱቫሉ፣ ቫኑዋቱና የመን ናቸው።

አንዳንድ ተመራማሪዎች ምናልባት እነዚህ አገራት በቂ ፍተሻ አላደረጉ ይሆን? ሲሉ ይጠረጥራሉ። ወይም ደግሞ ሙልጭ አድርገው እየካዱ ይሆን? ወይም ደግሞ ሪፖርት ተደርጎ አያውቅባቸውም ማለት ነው።

የሚገርመው ብዙዎቹ አገሮች ትንንሽ ደሴቶች መሆናቸው ነው። እነዚህ አገሮች ደግሞ እምብዛምም የውጭ አገር ጎብኚ የማይሄድባቸው አይደሉም።

እንደተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ በዓለም በጎብኚ ቁጥር የመጨረሻዎቹ 10 አገራት (ማለትም በዓመት ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚጎበኟቸው አገራት) በኮሮናቫይረስ አልተያዙም።

በቂ ርቀትን መጠበቅ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል አንዱ መንገድ ነው ሲባል ሰምተናል። እነዚህ ደሴቶች በአፈጣጠራቸውም ነጠል ብለው ነው የተወለዱት።

ለምሳሌ በፓሲፊክ ውቅያኖስ የሚገኘው ናዉሩ ደሴት በአቅራቢያው ከሚገኝ አገር በ320 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ባናባ ደሴት ነው ለናዉሩ ቅርቡ ጎረቤት አገር።

ናውሩ ደሴት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ተርታ ከሞናኮ ቀጥሎ ሁለተኛው ትንሹ ደሴት ሲሆን ጠቅላላ ሕዝቡ ከ10ሺህ አይበልጥም።

ድሃዋ ናውሩ የኮሮናቫይረስ ከተከሰተባት ከባድ አደጋ እንደሚሆን ተሰግቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ድሃዋ ናውሩ የኮሮናቫይረስ ከተከሰተባት ከባድ አደጋ እንደሚሆን ተሰግቷል

በዓለም ጎብኚዎች ድርሽ ከማይሉባቸው አገራት አንዱ ነው ናዉሩ። አንድ በአስጎብኚነት የተሰማራ መኮንን በዚያች ደሴት ባለፈው ዓመት የጎብኚዎች ቁጥር 160 ብቻ ነበር ብሏል፤ ይህ ቁጥር በሌላ ይፋዊ ጥናት ባይደገፍም ቅሉ።

ታዲያ እንዲህ ያለ አገር ራሱን በተፈጥሮ ቀድሞውኑ አርቆ ሳለ ምን መጠንቀቅ ያሻዋል ይባል ይሆናል። ሆኖም ነገሩ ወዲህ ነው።

በዚህ ደሴት አይበለውና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቢገባ ጉድ ነው የሚፈላው። አንድ ሆስፒታል ነው ያላቸው፣ አንድም የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ቬንትሌተር ላይኖራቸው ይችላል። የነርሶች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ስለዚህ ኮሮናቫይረስ ምናልባት ብዙ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል ማለት ነው።

የሆነስ ሆነና ይህቺ ናውሩ ደሴት ራሷን እንዴት ጠበቀች?

ከአንድ ወር በፊት ከቻይና፣ ከደቡብ ኮሪያና ከጣሊያን ማንም አይምጣብኝ አለች። ድሮም የሚመጣ አልነበረም ለነገሩ።

በመጋቢት ወር አጋማሽ ደግሞ ናውሩ ወደ ፊጂ ደሴት ወደ ኪሪባቲና ማርሻል ደሴቶች መብረር አቁሚያለሁ አለች። ወደ ጎረቤት ብሪስበን ብቻ በ15 ቀን አንድ ጊዜ እበራለሁ አለች።

ከዚያ በኋላም ከአውስትራሊያ ተመላሽ የሆኑ ሁሉ የ14 ቀናት ራስን የማግለል የውዴታ ግዴታ መመሪያን አወጣች።

እነዚህ ናዉሩን የመሰሉ ትንንሽ ደሴቶች እንኳንም ኮሮናቫይረስ በራቸውን አላንኳኳ ይላሉ ዶ/ር ኮሊን። ዶ/ር ኮሊን የቀድሞው የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ናቸው።

"እነዚህ አገሮች አንዳችም ሁነኛ የጤና ጥበቃ መዋቅር የላቸውም። ኮሮናቫይረስ ቢገባ ይንኮታኮታሉ፤ ቬንትሌተር እንኳ የላቸውም"› ይላሉ ዶክተሩ።

በዚያ ላይ በእነዚህ ደሴቶች የሚኖሩ አብዛኞቹ ዜጎች ስኳር፣ ደም ግፊትና ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎች አሉባቸው። ኮሮናቫይረስ በሽታ ያለበትን ሰው ምን እንደሚያደርግ ይታወቃል።

እንደ ዶ/ር ኮሊን ገለጻ እነዚህ ትንንሽ አገራት ሰው ሲታመምባቸው ወደ ውጭ አገር ነው የሚልኩት። አሁን ደግሞ ውጭ አገራት በራቸውን ከርችመዋል። በሽታው በእነዚህ ደሴቶች ገባ ማለት ሕዝባቸውን ጨረሰው እንደማለት ነው ይላሉ።

ስለዚህ የእነዚህ ደሴቶች ብቸኛ ተስፋ ተፈጥሮ ፈንጠር አድርጎ ፈጥሯቸዋልና ፈንጠር ብለው በራቸውን ከርችመው መኖር ብቻ ነው።

የናዉሩ ደሴት ፕሬዝዳንት ሊዮኔል አንጊሚያ አጥባቂ ሃይማኖተኛ ናቸው።

"ስለበሽታው ስሰማ ወደ እግዚያብሔር እጄን ዘረጋሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን አቀበለኝ። ወደ ደረቴ ጥብቅ አድርጌ ያዝኩት፡፡ መዝሙር ዳዊት አንቀጽ 147፣ ምን ይላል።

"ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በይ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቷልና፥ ልጆችንም በውስጥሽ ባርኳልና። በወሰንሽም ሰላምን አደረገ"

ፕሬዝዳንቱ ቀጠሉ፤

"በየጊዜው የዓለምን ካርታ ከፍቼ የበሽታውን ስርጭት ስመለከት አገሩ ምድሩ ሁሉ በፈንጣጣ የተያዘ ይመስል ቀይ በቀይ ሆኗል። ስለዚህ እኛ ናዉሩዎች ለተቀረው ዓለም መጸለይ እንዳለብን ይሰማናል። ጸሎታችን እንደሚረዳችሁም ተስፋን እናደርጋለን።"

የኮሮናቫይረስን ሽሽት ሻንጣችንን እንሸክፍ ይሆን? ወደ ናዉሩ ደሴት!

ኮሮና
Banner