አሜሪካ፤ አምስት የቻይና የሚዲያ ተቋማት ላይ እገዳ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ፤ መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ የቻይና የዜና አውታሮች ላይ አዲስ እገዳ የጣለች ሲሆን ይህ የዜና ተቋማቱ የአሜሪካ ሰራተኞቻቸውን በግማሽ እንዲቀንሱ ግድ ይላል።
ይህ የአሜሪካ እርምጃ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቤጂንግ ሁለት የአሜሪካ ጋዜጠኞችን ለማስወጣቷ የተሰጠ የአፀፋ ምላሽ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
በዚህ አሜሪካ በጣለችው አዲስ እግድ አምስት የቻይና የሚዲያ ተቋማት ሰራተኞቻቸውን 40 በመቶ ለመቀነስ እንደሚገደዱ ተገልጿል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሶቪየት ህብረት እንኳ ያላደረገችውን የመናገር ነፃነት ገደብን እያደረገች ነው ሲሉ ቻይናን እየወነጀሉ ነው።
በቻይና የሚሰሩ የአሜሪካና የሌሎች አገራት ጋዜጠኞችን የማስፈራራትና የመሰለል ተግባርን ቻይና ስራዬ ብላ ተያይዛዋለችም ይላሉ የአሜሪካ ባለስልጣናት።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በሰጡት የፅሁፍ መግለጫ ታዋቂውን ዢንዋን ጨምር አምስት የቻይና የሚዲያ ተቋማት ከ100 እስከ 160 የሚደርሰውን የሰው ሃይላቸውን እንዲቀንሱ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።
ይህ የጋዜጠኞች ቁጥር ላይ የተደረገ ገደብ እንደ ቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ፣ ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና ሬድዮ ኢንተርናሽናልና ፒፕልስ ዴይሊን እንደሚመለከት ታውቋል።
የእነዚህ ሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች በአፋጣኝ አሜሪካን እንዲለቁ ባይደረግም ግን ስራቸውን መሰረት አድርጎ የተሰጣቸው ቪዛን ጥያቄ ውስጥ እንደሚጥል አጠራጣሪ እንዳልሆነ እየተነገረ ነው።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት እገዳ ፍፁም ያልተጠበቀ እንደሆነ አስተያየት እየሰጡ ያሉ አሉ። እገዳው ተፈፃሚ የሚሆንባቸው አምስቱ የቻይና ሚዲያ ተቋማት የቻይና መንግሥት ሁነኛ የፕሮፖጋንዳ ተልእኮ መሳሪያዎች ናቸው ትብሎ የሚታመኑ ናቸው።
ቻይና በውጭ አገር ሪፖርተሮች ላይ ለዓመታት የቪዛ እገዳ ስትጥል መቆየቷን በመጥቀስ የአሁኑ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ቀደም ማለት የነበረበት የሚሉ አሉ።
የፖምፒዮ የጨዋታ ሜዳውን በቻይናም በአሜሪካም በኩል አንድ አይነት የማድረግ ውሳኔ ቀደም ብሎ መምጣት የነበረበት የሚለው ንግግርም ከላይ ያለውን ሃሳብ ያጠናክራል።












