የዓለም አክስዮን ገበያ በኮረናቫይረስ እየተቃወሰ መሆኑ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአክስዮን ገበያ ከአውሮፓውያኑ የ2008 የዓለም የገንዘብ ቀውስ ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መቃወሱ ተነገረ።
በእስያ የተቀሰቀሰው ኮረናቫይረስ አውሮፓ መድረሱን ተከትሎ የእስያ ገበያዎች በአክስዮን ገበያ መናጋት ክፉኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል።
የዋልስትሪት ዶጆንስ ሰንጠረዥ ትናንት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዝቅተኛ ነጥብ ተመዝግቦበታል። ተመሳሳይ የአክስዮን ገበያ ማሽቆልቆል በጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ ኮሪያና ቻይና የአክስዮን ገበያዎች የተመዘገበ ሲሆን ይህም ባለሃብቶችን ክፉኛ እንደጎዳ ተገልጿል።
በተለይም የኮረናቫይረስ በጣልያን መቀስቀስ ከተገመተው በላይ ቫይረሱ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተፅእኖ ሊያሳሰድር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የቻይናው እውቅ የኢኮኖሚ ባለሙያ ኢሪስ ፓንግ "ገበያዎቹ በጣም ተስፋ ነበራቸው፤ አሁን ግን በጣም ተስፋቢስ ሊሆኑ ይችላሉ" ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
የኢኮኖሚ ተንታኙ እንደሚሉት መጀመሪያ ላይ ኮሮናቫይረስ የቻይና ችግር ብቻ እንደሚሆን ተገምቶ ስለነበር የእስያ ገበያ ብዙም በኮረናቫይረስ አልተቃውሰም ነበር።
ነገር ግን ቫይረሱ ጎረቤት ደቡብ ኮሪያን ሲያንቀጠቅጥ እንዲሁም ጃፓንን ክፉኛ ሲያሰጋ የአህጉሪቱ ገበያ የኮረናቫይረስ ወላፈን ያቃጥለው ጀመር።
በሌላ በኩል ኮረናቫይረስ እንደተቀሰቀሰ ወዲያው ተናግቶ የነበረው የእስያ አክስዮን ገበያ መልሶ መረጋጋት ችሎ ነበር፤ ዳግም አሁን እስኪናጋ ድረስ።
ነገሮች አሁን እየሄዱ ባለበት ሁኔታ የቫይረሱን ስርጭት እንዴት መግታት ይቻላል የሚለው እስካልታወቀ ድረስ ኮረናቫይረስ ዓለምዓቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተፅእኖን መገመት ከባድ እንደሆነ ነው የኢኮኖሚ ተንታኞች እየገለፁ ያሉት።












