የካቶሊኩ ፖፕ ለቄሶች ማግባት ይፈቅዱ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, AFP
በመላው አለም የሚገኙ የካቶሊክ ካህናት በቤተክርስቲያኗ ዕጣ ፈንታ ላይ ከሰሞኑ ይመክራሉ።
በሚቀጥሉትም ሦስት ሳምንታት 260 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ፣ ስደትና ስለ ኢቫንጀላውያን እንቅስቃሴ የሚወያዩ ሲሆን ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ቤተክርስቲያኗ ላገቡ ወንዶች የቅስና ማዕረግን ልትፈቅድ ትችል ይሆን ወይ የሚለው ነው።
ስብሰባው በአማዞን የሚካሄድ ሲሆን ሸምገል ያሉና ያገቡ ወንዶች ቄስ እንዲሆኑ እንዲፈቀድላቸውም አንድ ረቂቅ ፅሁፍ መዘጋጀቱም ተጠቅሷል።
በረቂቁ መሠረት ከዕድሜያቸው በተጨማሪ በማሕበረሰቡ ዘንድ አንቱታን ያገኙና የአገሬው ተወላጅና በአካባቢው ለመስራት ፈቃደኛ መሆን አለባቸው ተብሏል።
በደቡብ አሜሪካ ያለውን የካህናት እጥረት ለመቅረፍም ስለሚያስችል የአካባቢው ጳጳሳት ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው።
በቅዳሴ ሥነ ስርዓት ላይ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የማቁረብ ተግባር (የኢየሱስን ስጋና ደም ለምዕመናን ማቀበል) የሚችሉት ቄሶች ብቻ ናቸው።
በአማዞን መንደሮች ውስጥ ከሚገኙት ማህበረሰቦች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት በካህናት እጥረት ምክንያት መቁረብም ሆነ ቅዳሴውን መከታተል የሚችሉት በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው ተብሏል።
ፖፕ ፍራንሲስ ትውልዳቸው ላቲን አሜሪካ ከመሆኑ አንፃር የቀጠናው ችግርን በበለጠ ሊረዱት እንዲሚችሉ በካቶሊክ ጥናት ማዕከል ፕሮፌሰር ግሪጎሪ ራያን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
በካቶሊክ እምነት ዘንድ ቄሶች ከወሲባዊ ግንኙነት መታቀባቸውና አለማግባታቸው ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። አለማዊ ሕይወታቸውን ቤተሰብም ሆነ ሚስትን ሳይሉ ሙሉ ሕይወታቸውን ለፈጣሪያቸው ሊሰጡ ይገባል በሚልም ነው ቤተክርስቲያኗ ጋብቻን የምትከለክለው።
በሃይማኖቶች ላይ ከፍተኛ ጥናት ያደረገችው ፕሮፌሰር ሊንዳ ከጋብቻ ክልከላ በተጨማሪ የካቶሊክ ካህናትና መነኮሳት ቤትና የተወሰነ ገንዘብ ተሰጥቷቸው የምነና አይነት ሕይወት የሚኖሩበት ነው ትላለች።
ለምዕመናኑም በሚፈለጉበት ወቅት ማንኛውንም አይነት አገልግሎት ለመስጠትም ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግም እንዳለባቸው ቤተ ክርስቲያኗ እንደምታዝም ገልጻለች።
ለወግ አጥባቂዎቹ ይህ ጉዳይ የሚዋጥ አልሆነም፤ የጀርመኑ ካርዲናል ዋልተር ብራንድሙለር እንዳሉት "ቤተ ክርስቲያኗ ለራሷ ጥፋት እየሰራች ነው" በማለት ጠንከር ያለ ትችት አቅርበዋል።
በአማዞን ካህናት ማግባት ከተፈቀደላቸው ሌሎችም አካባቢዎችስ የማይፈቀድበት ምክንያት ምንድን ነው? በማለት የቤተክርስቲያኗ ሥር ነቀል ለውጥ ሊሆን እንደሚችልም እየተነገረ ነው።
ለአንዳንዶች ቤተክርስቲያኗ እያለፈችበት ያለውን ተቋማዊ ለውጥ የሚያሳይ ነው ያሉ ሲሆን በተለይም ዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ትተችባቸው የነበሩ ነገሮችን እያሻሻለች ነው ተብሏል።
ያገቡ ካህናትን እናይ ይሆን?
አሁንም ያገቡ ካህናት አሉ።
የአንግሊካን እምነት ተከታይ የሆኑና ወደ ካቶሊክነት የተቀየሩ ያገቡ ቄሶች በማዕረጋቸው ቀጥለዋል።
እነዚህ ቄሶች በአንግሊካን እምነት ውስጥ ያለውን የሴትን ቅስና መፍቀድ ተከትሎ ነው ወደ ካቶሊክነት የተቀየሩት።
በአማዞን ጋብቻው ከተፈቀደ በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈፀም እንደሚችል የሚናገሩ ቢኖሩም አንዳንዶች ግን ከችግሩ አንፃር ነጥሎ መፍቀድ ይቻላል ብለው ይከራከራሉ።












