አንበሳዋ እናት፡ የልጃቸውን ደፋሪ የገደሉት እናት ነጻ ወጡ

ኖኩቦንጋ ኳምፒ በደቡብ አፍሪካ "አንበሳዋ እናት" በመባል የታወቁት ልጃቸውን ከደፈሩ ሦስት ወንዶች መካከል አንዱን ገድለው ሌሎቹን ካቆሰሉ በኋላ ነው። በግድያ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ቢሆንም በሕዝብ ድምፅ ምክንያት ክሱ ተነስቷል።
ነገሩ የጀመረው እኩለ ሌሊት ላይ የስልክ ጥሪ ኖኩቦንጋን ከእንቅልፍ ሲቀሰቅሳቸው ነበር። የደወለችውም ሴት ኖኩቦንጋ ሲፎካዚ የተባለችው ሴት ልጃቸው በሚያውቋቸው ሦስት ወንዶች መደፈሯን በዚያ ሌሊት ነበር የነገረቻቸው።
ኖኩቦንጋ የመጀመሪያ እርምጃቸው ፖሊስ መጥራት ነበር፤ ነገር ግን የፖሊሶቹ ስልክ አይመልስም። በጊዜው ልጃቸውን መርዳት የሚችሉት እራሳቸው ብቻ ነበሩ።
"በጣም ፈርቼ ነበር ግን ልጄ ናት፤ መሄድ ነበረብኝ" ይላሉ እናት ኖኩቦንጋ።
"እዚያ እስክደርስ ትሞታለች ብዬ አስቤ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ እኛን ስለሚያውቁን እንዳትናገር ፈርተው በሕይወት አይለቋትም ብዬ አስቤ ነው።"
በጊዜው ሲፎካዚ ጓደኞችዋን ለማግኘት ነበር እግሯን ወደዛች መንደር የመራቸው። በቆይታዋም ጓደኞችዋ በተኛችበት ለብቻዋ ጥለዋት በወጡበት አጋጣሚ ነበር የጠጡት ወንዶች ከተኛችበት ገብተው ጥቃት ያደረሱባት።
"ቢላ ይዤ የሄድኩት እራሴን እዚያ እስክደርስ ባለው መንገድ ላይ ለመከላከል ብዬ ነበር" ሲሉ ኖኩቦንጋ ሁኔታውን ያስታውሳሉ። "ከቢላው ጋር ስልኬን ለብርሃን ብዬ ይዤ ነበር።"
ልጃቸው ወደ ነበረችበት ቤት ሲደርሱ ስትጮህ ሰሟት፤ ቤት ውስጥ ሲገቡም አንዱ ወንድ ልጃቸውን ሲደፍራትና ሌሎቹ ሁለት ወንዶች ደግሞ ሱሪያቸው ወልቆ ተራቸውን ሲጠባበቁ እንዳኟቸው ይናገራሉ።
"በጣም ስለፈራሁ በር ላይ ቆሜ ምን እያደረጉ እንደሆነ ጠየኳቸው። እኔ እንደሆንኩ ሲያውቁ በቁጣ ተንደርድረው ወደ እኔ መጡ፤ ያኔ ነው እራሴን መከላከል እንዳለብኝ የገባኝ።"
ክሱን ሲከታተል የነበረው ዳኛ ኖኮቦንጋ ልጃቸው ስትደፍር በአይናቸው ማየታቸው "በጊዜው በጣም ስሜታዊ" አድርጓቸዋል ብለዋል።
ኖኩቦንጋም በጊዜው ይዘውት የነበረውን ቢላ በመጠቀም አንዱን ደፋሪ ገድለው ሌሎቹን በቆሰሉበት ትተው ልጃቸውን በቅርብ ወደ ሚገኝ ጎረቤት ወሰዷት።
ፖሊሶችም ከቦታው ደርሰው ቦኩቦንጋን በቁጥጥር ስር ካደረጓቸው በኋላ በአቅራቢያ ወደ ሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ወሰደወቸው።
"ስለ ልጄ እያሰብኩ ነበር፤ ካዳንኳት በኋላ ስለእሷ ምንም አልሰማሁም። በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነበር" ይላሉ።

እናትዋ ወደ እስር ቤት ሲወሰዱ ሲፎካዚ ሆስፒታል ሆና ስለእናትዋ እያሰበች ነበር። "በፍርድ ቤት ተወስኖባት ለዓመታት የምትታሰር ከሆነ እኔ ቅጣቷን እቀበልላታለሁ እያልኩኝ አስብ ነበር" ትላለች።
ሲፎካዚ በጊዜው ስለተፈጠረው ነገር እናትዋ ከነገሯት ነገር ውጪ ምንም አታስታውስም ነበር። በጊዜውም እናትና ልጅ አንዳቸው የአንዳቸው ደጋፊ ነበሩ።
ቡህሌ ቶኒስ የኖኩቦጋ ጠበቃ ስትሆን ከጥቃቱ አንድ ሳምንት በኋላ ስታገኛቸው እናትና ልጅ በጣም ተስፋ ቆርጠው እንደነበር ታስታውሳለች።
"ኖኩቦንጋ በጭንቀት ውስጥ ነበረች" ትላለች።
"በጣም ድሃ የሆኑ ሰዎችን ስታገኚ ገንዘብ ስለሌላቸው እናትየዋ ወደ እስር ቤት የምትሄድ ይመስላቸዋል። ይህ ደግሞ ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው አለ ብለው ሰለማያስቡ ነው።"
ቡህሌ ኖኩቦነጋ ክሱን ማሸነፍ እንደምትችል እርግጠኛ ብትሆንም ቀላል እንደማይሆን ገምታለች። ሁለቱም ግን ያልጠበቁት ነገር ቢኖር የማህበራዊ ሚዲያ የሚያደርግላቸውን ድጋፍ ነበር።
በደቡብ አፍሪካ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ብዙም የማህበራዊ ሚዲያ ሽፋን አይሰጣቸውም፤ ነገር ግን የኖኩቦንጋ ድርጊት እናት ልጇን ለመከላከል ያላትን አቋም ማሳያ ነው በማለት የማህበራዊ ሚዲያውን ቀልብ ሳበ።
የልጃቸውን ማንነት ላለመግለፅ ሲባል የኖኩቦንጋን ስም መጥቀስ ባልተቻለበት ጊዜ አንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም "አንበሳዋ እናት" ብሎ ምስላቸውን ሴት አንበሳ ከልጆችዋ ጋር አድርጎ ይፋ አደረገው። ይህም ስም በመላ አገሪቷ አስተጋባ።
"መጀመሪያ ስሙን ስሰማ አልወደድኩትም ነበር፤ ልክ ግን የጀግንነት ምሳሌ መሆኑን ሳውቅ በጣም ደስ አለኝ" ይላሉ እናት።
የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ የኖኩቦንጋን ክስ በመተቸት የህግ አማካሪ ጠበቃ እንዲኖራት ገንዘብ አሰባሰቡ።
"ወደ ፍርድ ቤት ስሄድ ስለፈራሁ ጠዋት ተነስቼ ፀለይኩኝ" ይላሉ።
ኖኩቦንጋ ፍርድ ቤት ሲደርሱ በሰዎች ተሞልቶ ነበር ያገኙት። "ከመላዋ ደቡብ አፍሪካ የተሰባሰቡ ሰዎች ነበሩ። ለሰዎቹ አመሰግናለሁ እያልኩኝ እነሱ ሊደግፉኝ በመምጣታቸው በተስፋ ተሞላሁ።"
"ፍርድ ቤት ስደርስ ክሱ እንዲነሳ ተወሰነ። በጣም ደስ አለኝ፤ ያኔ ዳኛው እኔ ሰውን የመግደል ሃሳብ እንዳልነበረኝ እንደተረዳ ገባኝ።"
ቡህሌ ቶኒስ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲፎካዚ ላይ የፈጠረውን ስሜት ታስታውሳለች። "ፍርድ ቤቱ ክሱን እንዳነሳ ኖኩቦንጋ ወደ ልጇ ደወለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ሲፎካዚ ስትስቅ የሰማኋት ያኔ ነበር። እሷም ለእናትዋ ወንዶቹ እንዲታሰሩ እንደምትፈልግም ነገረቻት" ትላለች።
ይህ ፍላጎቷ እውን እንዲሆን ከዓመት በላይ መጠበቅ ነበረባቸው። ከዚያም ባለፈው የታህሳስ ወር ላይ ሁለቱ ወንጀለኞች የ30 ዓመት እስራት ተወሰነባቸው።
ሲፎካዚ "በውሳኔው ደስተኛ ነኝ፤ አሁን ደህንነት ይሰማኛል ነገር ግን የእድሜ ልክ እስራት ይገባቸው ነበር" ትላለች።
ልክ ክሱ ሲጠናቀቅ ሲፎካዚ ሌሎች የዚህ ዓይነት ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ለመደገፍ በማለት ማንነትዋን ለህዝብ ይፋ አድርጋለች።
ኖኩቦነጋ በበኩላቸው በሚያስገርም ሁኔታ ልጃቸውን የደፈሩት ሰዎች ወደፊት ከእስር ሲወጡ መልካም ነገር ያደርጋሉ፣ ምሳሌም ይሆናሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።












