ዩጋንዳ ሰራዊቷ የቻይና የንግድ ቦታዎችን እንዲጠብቅ አዘዘች

የዩጋንዳ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቻይና ኩባንያዎች ላይ የሚደረጉ ዝርፊያዎችን ተከትሎ የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ሰራዊቱ እንዲጠብቅ ትዕዛዝ ሰጡ።

ፕሬዚዳንት ዩዎሪ ሙሴቬኒ ረቡዕ ዕለት 120 የሚሆኑ የቻይና ኢንቨስተሮችን ባናገሩበት ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር እንደሚደረግና የሲሲቲቪ ካሜራዎችም እንደሚገጠሙ ገልፀዋል።

ቻይና በዩጋንዳ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ ብታፈስም ከፍተኛ በሆነ ዝርፊያ ምክንያት ብዙ ገንዘብ እንደምታጣም ተገልጿል።

በዚህም ነው መንግሥት በአገሪቱ ያለውን ወንጀል ለማስቆም ጥበቃውን እንዲያጠናክር ግፊት የበዛበት።

"ለኔ ይህ ችግር ቀላል ስለሆነ ይፈታል" በማለትም ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ጨምረውም የቻይና የንግድ ቦታዎችን እየጠበቁ የጦር መሳሪያቸው ለሚጠፋባቸው የጥበቃ ሰራተኞች ወታደራዊ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ያስጠነቀቁ ሲሆን ይህን ያሉት በዝርፊያዎቹ ላይ የጥበቃ ሰራተኞችም ተሳታፊ ናቸው የሚል ጥርጣሬዎ ስላለ ነው።

በዚህ እርምጃ ፕሬዚዳንቱ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን ገሸሽ አድርገው የውጭ ኩባንያዎችን ለመጠበቅ ቅድሚያ ሰጥተዋል በሚል እያስተቻቸው ነው።

የቢቢሲዋ ካትሪን ቢያሩንጋ ከመዲናዋ ካምፓላ እንደተናገረችው በከፍተኛ ሁኔታ ግድያዎችና ዝርፊያዎች የመሳሰሉ ወንጀሎች መጨመራቸው የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

የዩጋንዳ መንግሥት ለችግሩ ምላሽ የሰጠው በመዲናዋ ካምፓላና በአካባቢው እየተዘዋወሩ የሚጠብቁ የፀጥታ ሃይሎችን እንዲሁም መደበኛ ዜጎችንም በተመሳሳይ ለጥበቃ በማደራጀትና የሲሲ ቲቪ ካሜራዎችን በየቦታው በመግጠም ነው።