በሞያሌ በሶማሌና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል በተከሰተ ግጭት የ19 ሰዎች ህይወት አለፈ

የሞያሌ ከተማ

ካለፈው እሁድ ጀምሮ ሞያሌ ከተማ ሰላም እርቋታል። ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት እንደሰማነው፤ በይዞታዎች ይገባኛል ምክንያት በኦሮሞ እና ሶማሌ ታጣቂ ሚሊሻዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ የ19 ሰው ሕይወት አልፏል፣ 102 ሰው ቆስሏል።

የሞያሌ ወረዳ ጤና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ቦሮ ሆቃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በኦሮሚያ ወገን 6 ሰዎች ሲሞቱ 72 ደግሞ ቆስለዋል።

በሶማሌ ክልል በደህንነት አማካሪነት የሚሰሩት አቶ ሸኑ ጎደኖ ደግሞ ከሶማሌ ወገን 13 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 30 መቁሰላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ቦሩ እንደሚሉት ከሆነ በግጭቱ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ በጥቅም ላይ ውሏል።

የሞያሌ ወረዳ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ጠቼ ግጭቱ መነሳቱን አምነው ግጭቱ ግን የጎሳ ሳይሆን በሶማሌ በኩል የመሬት መስፋፋት ፍላጎት ስለነበረ ነው ሲሉ ከሰዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ የሶማሌ ክልል ሞያሌን ወደ ዞን ለማሳደግና የዞኑ ከተማ መቀመጫም ለማድረግ ፍላጎት አለው ሲሉ ይከሳሉ። ይህንንም ለክልልና ለፌደራል መንግስት አመልክተው ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ።

አቶ አሊ ጠቼ ጨምረውም በግጭቱ የአንድ ትምህርት ቤት ሁለት ክፍሎች እና የጤና ኬላ መቃጠሉን ተናግረዋል።

አቶ ሸኑ ጎደኖ በበኩላቸው የግጭቱ መንስዔ በኦሮሞዎች በኩል የመሬት መስፋፋት ፍላጎት በመኖሩ ነው ሲሉ ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው አባባል ከዚህ በፊት ሁለቱ ህዝቦች የይገባኛል ጥያቄ ያነሱባቸው በነበሩ አካባቢዎች የኦሮሞ ተወላጆች መጥተው ባንዲራ መትከላቸው እንደሆነ ጨምረው አስረድተዋል።

ባንዲራውን የተከሉት በሶማሊያ መሬት ላይ ጭምር እንደሆነ የገለፁት አቶ ሸኑ 'ባንዲራ ንቀሉ አንነቅልም' በሚል እሰጥ አገባ ግጭቱ መነሳቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።