የ7 ዓመቷ ህጻን ግድያ፡ ''ከልክ ያለፈ ቅጣት የልጄን ህይወት አሳጣኝ'' የእምነት ክህደት ቃል

የፎቶው ባለመብት, Woizer Sehen Poly Technic College Facebook
በደሴ ከተማ የሰባት ዓመት ልጅ ሬሳ በማዳበሪያ ተጠቅልሎ የተገኘው ጥቅምት 27፣ 2010 ዓ. ም ነበር። የልጅቷ አሟሟት ያስቆጣቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም ንዴታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።
በወቅቱ ልጅቷን ገድሏል በሚል የተጠረጠረው የልጅቷ የእንጀራ አባት በቁጥጥር ስር ውሏል። ሕዝቡ "ተጠርጣሪውን አሳልፋችሁ ስጡን" በማለት ቁጣውን አሰምቶ ነበር።
የደሴ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ደረጄ አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ተጠርጣሪ ተብሎ የታሰረው የእንጀራ አባቷ ቢሆንም፤ የፖሊስ ምርመራን ተከትሎ የልጅቷ ገዳይ እናቷ ልትሆን እንደምትችል ተጠርጥሮ እናትየዋ በቁጥጥር ስር ውላለች።
የልጅቷ እናት ትላንት ፍርድ ቤት የቀበረች ሲሆን፤ የእምነት ክህደት ቃሏን ሰጥታ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተወስኗል። ለእንጀራ አባቷ ደግሞ ሰባት ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ኮማንደሩ እንደተናገሩት፤ የልጅቷ መጥፋት ለፖሊስ ሪፖርት የደረሰው ጥቅምት 24፣ 2011 ዓ. ም ነበር። የልጅቷ እናት አበባ ሙህዬ ዳውድ፤ በጸሎት ብርሀኑ የምትባል ልጇ ሰፈር ውስጥ ትጫወት ከነበረበት እንደተሰወረች ለፖሊስ ተናግራለች።
ጥቅምት 27፣ 2011 ዓ. ም ከኡራኤል ቤተክርስቲያን ከፍ ብሎ የልጅቷ ሬሳ በአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝቶ ወደ ደሴ ሆስፒታል ተወሰደ።
እናትየዋ፤ አቡበከር ሙሀመድ አህመድ ከተባለ አጋሯ የወለደቻትን ልጅ ለማሳደግ አቅም ስለሌላት የ40 ቀን ጨቅላ ሳለች ለጓደኛዋ ቤተሰቦች መስጠቷን ለፖሊስ ተናግራለች።
በሁኔታው የፍቅር ጓደኛዋ ተበሳጭቶ "ልጄን እንደጣልሻት ያንቺንም ልጅ ወስጄ እጥላለሁ" ብሎ እንደዛተባት ለፖሊስ ተናግራም ነበር።
የልጅቷ አስክሬን ወደ አዲስ አበባ ለምርመራ ከተላከ በኋላ በምርመራው ወቅት "የልጅቷ እጅና እግሯ መታሰር፣ በወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ሬሳዋ መጠቅለሉ ምርመራውን ወደ እናትየዋ እንዲያመራ አደረገው" ይላሉ ኮማንደር ደረጄ።
እናትየዋ በወቅቱ ሀዘን ተቀምጣ ነበር። ፖሊሶች ስለወንጀሉ ሲጠይቋት የእምነት ክህደት ቃሏን መስጠቷንም ኮምንደሩ ተናግረዋል።
እናትየዋ ለፖሊስ እንዳሳወቀችው ከሟች ልጇ ጋር በመሆነ አራዳ ተብሎ በሚጠራው ገበያ ስትገበያይ ነበረ። ልጇም ጫማ እንዲገዛላት ጠየቀቻት። እናት 'አቅም የለኝም' በማለት መልስ ብትሰጣትም፤ ልጅቷ ግን መጠየቋን አላቆመችም። ቤት ከደረሱም በኋላም የልጅቷ ጥያቄ ሲቀጥል በንዴት በዘነዘና እንደመታቻት ለፖሊስ ተናግራለች።
በእናትየው ለፖሊስ በሰጠችው ቃል መሰረት የልጅቷ ህይወት ያለፈው ወዲያው ነበር። እናትየዋ ለፖሊስ "ልጄ ጠፋች" ብላ ባመለከተችበት ተመሳሳይ ቀን የልጇን አስክሬን መጣሏን እንዳመነች ኮማንደሩ ገልጸዋል። ''ከልክ ያለፈ ቅጣት የልጄን ህይወት አሳጣኝ'' እንዳለችም ኮማንደሩ አክለዋል።
እንትየዋ ከአጋሯ ጋር ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ አብራ ትኖር የነበረ ቢሆንም፣ በመካከላቸው አለመግባበት በመፈጠሩ እንደተለያዩ ኮማንደሩ ተናግረዋል።
የልጅቷ ሬሳ ሲገኝ "ተደፍራለች፤ ሰውነቷ ተቆራርጧል" የሚል ያልተገጋገጠ ወሬ መሰራጨቱን ኮማንደሩ አስታውሰው፤ የአስክሬን ምርመራ ውጤቱ ገና በእጃቸው ባይገባም፤ ሬሳዋ ሲገኝ ሰውነቷ ላይ ችግር እንዳልደረሰ ገልጸዋል።
ሆኖም የተሳሳተ መረጃ መሰራጨቱ በሕዝቡ ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል። በተሳሳተ መረጃ ፖሊሶች ላይ ጠቃት ተሰንዝሮ እንደነበረ የገለጹት ኮማንደሩ፤ በፖሊስ አባላት ላይ በተወረወረው ድንጋይ ስምንት አባላት ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ኮማንደሩ ተናግረዋል።












