የማይናማር ግጭትን ለማባባስ ፌስቡክ ጥቅም ላይ መዋሉን ሪፖርት ጠቆመ

የማይናማር ግጭትን ለማባባስ ፌስቡክ ጥቅም ላይ ውሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የማይናማር ግጭትን ለማባባስ ፌስቡክ ጥቅም ላይ ውሏል

ፌስቡክ የማይናማር ግጭትን ለማባባስ ጥቅም ላይ እንዳይውል መከላከል ተስኖታል የሚለውን ሪፖርት ፌስቡክ እንደሚስማማበት ገልጸ።

በፌስቡክ የተዋቀረው ገለልተኛ ሪፖርት እንደጠቆመው በማይናማር የመብት ጥሰቶችን እና ግጭቶችን ለማባባስ ፌስቡክ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

የተባበሩት መንግሥታት፤ በሮሂንጋ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰውን ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት "ለዘር ማጥፋት የቀረበ" ሲል ፈርጆት ነበር።

ፌስቡክ በማይናማር ከ18 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት። ፌስቡክ ለበርካቶች ዋነኛው ወይም ብቸኛው የመረጃና የዜና ምንጭ ነው።

የፌስቡክ አስተዳደሮች "በማይናማር እየገጠመን ያለውን ችግር ለመቅረፍ እየሠራን ነው። ሆኖም ብዙ ይቀረናል'' ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የሮሂንጋ ታጣቂዎች ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የሃገሪቱ ጦር ራክሂን በምትባለው ግዛት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር።

በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ወደ ጎረቤት ሃገር ባንግላዲሽ ተሰደዋል። በሮሂንጋውያን ላይ የአስገድዶ መድፈር፣ የእርሻ መሬትን መቃጠልና መሰል በደሎች ደርሶባቸዋል።

ሮሂንጋውያን በማይናማር (በርማ ተብላ ትጠራ በነበረው) ሃገር ውስጥ እንደ ስደተኛ ይቆጠራሉ። በመንግሥት እና በተቀረው ሕዝብ ለበርካታ አስረት ዓመታት ተገልለዋል።

ቢዝነስ ፎር ሶሻል ሪስፖንሲቢሊቲ (Business for Social Responsibility -BSR) ያቀረበው ባለ 62 ገጽ ገለልተኛ ሪፖርት ''በማይናማር ግጭትና ጥላቻን ማባባስ ለሚፈልጉ ቡድኖች ፌስቡክ መጠቀሚያ ሆኗል'' ይላል።

ሪፖርቱ፤ ፌስቡክ የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ያለውን ፖሊሲ እንደገና ሊከልሰው ይገባል ሲልም አክሏል።