ከደብረ ብርሃን 12 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ጫጫ ከተማ በደረሰ የመኪና አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Ankober Communication/Facebook
ከደብረ ብርሃን 12 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው በጫጫ ከተማ በደረሰ የመኪና አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት አልፏል።
አደጋው የደረሰው ዛሬ ነሐሴ 8 2010 ዓ.ም በግምት ከቀኑ ስድስት ሰአት አካባቢ ሲሆን ቅጥቅጥ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪና ሲኖትራክ ተጋጭተው መሆኑም ተገልጿል።
የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን በመጓዝ ላይ የነበረ ሲሆን በተቃራኒው ሲኖትራክ ደግሞ ከደብረብሃን ወደ አዲስ አበባ መስመር እየተጓዘ ነበር።
አስራ ሁለት ሰዎች ወዲያውኑ በቦታው ህይወታቸው ሲያልፍ፤ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት ደግሞ አራቱ ደብረብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸው ማለፉን የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ዳግም አጣለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ 11 ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በደብረብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
ከተሳፋሪዎች መካከልም አራት ህፃናት ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በህይወት መትረፍ ችለዋል።
የአደጋው ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ገና ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና የህዝብ ማመላለሻው ተሽከርካሪ ምን ያህል ተሳፋሪዎችን ጭኖ እንደነበረም እርግጠኛ መሆን ዋና እንዳልቻሉ ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።














