በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ ሰርቲ ቀበሌ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ18 ሰዎች ህይወት አለፈ

ግጭት የደረሰባቸው ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Amhara Police Face Book

አደጋው ለሐይማኖታዊ በዓል ጻድቃኔ ማሪያም ሄደው የነበሩ ምዕመናንን አሳፍሮ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሀን ሲጓዝ ከነበረ ሚኒባስ ጋር በመጋጨቱ የደረሰ ነው።

በአደጋው ወዲያውኑ የ13 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 5ቱ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸው ማለፉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ አስተባባሪ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር መንገሻ አውራሪስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከሟቾቹ መካከል አራቱ ሴቶች መሆናቸውን የአንጎለላ ጠራ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ዳግም አጣለ ነግረውናል።

አውቶቡሱ ዳገት እየወጣ ሚኒባሱ ደግሞ ቁልቁለት እየወረደ እንደነበር የተናገሩት ኢንስፔክተሩ በስፍራው ለአደጋ የሚያጋልጥ እይታን የሚከለክል ምንም ነገር እንዳልነበር አስረድተዋል።

ነገር ግን አውቶቡሱ መንገዱን ለቆ በቀኝ መስመር መሄድ ሲገባው በግራ መስመር ላይ እየተጓዘ እንደነበር ተናግረዋል፤ በአደጋውም በሚኒባሱ ተሳፋሪዎች ሙሉ በሙሉ ህይወታቸው እንዳለፈም ጨምረው ገልፀዋል።

አደጋው ትናንት ማክሰኞ ከቀኑ 10፡30 ላይ እንደደረሰ የገለፁት ዋና ኢንስፔክተር መንገሻ በበኩላቸው እስከ ምሽቱ 4፡00 ሰዓት ድርስ የአደጋው ተጎጂዎችን ለማውጣት መንገድ ተዘግቶ እንደነበር አስታውቀዋል።

ኢንስፔክተሩ በክልሉ የሚደርሱ አብዛኞቹ የትራፊክ አደጋዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር እንደሆነም ተናግረዋል።

በክልሉ ለአደጋ አስጊ በሆኑ ቦታዎች አደጋዎች ሲከሰት አይታዩም የሚሉት ኢንስፔክተር መንገሻ አሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከራቸው ለሚደርሱ አደጋዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር እጥረት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።