"400 ሚሊዮን ዶላር ካሳ" ለወርቅ ቆፋሪዎች

"400 ሚሊዮን ዶላር ካሳ" ለወርቅ ቆፋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካ ብልጽግና በወርቅ ማዕድን የተለበጠ ነው። የሚያብረቀርቀው ወርቅ የጥቁር አፍሪካዊያን ጨለማ ሕይወት ሳይጋርደው አልቀረም።

ወርቅ ቆፋሪ የጉልበት ሠራተኞች ለምዕተ ዓመት ያህል ለከፋ የጤና ችግር ሲጋለጡ፣ በማይድኑ በሽታዎች ሲያጣጥሩ የወርቅ ኩባንያዎቹ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ቆይተዋል።

ሰሞኑን ግን ያልተጠበቀ የፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰምቷል። ኩባንያዎቹ ካሳ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ዉሳኔ።

በደቡብ አፍሪካ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወርቅ ቆፋሪ የጉልበት ሠራተኞች እጅግ አደገኛ ለሆነ የሳንባ በሽታ ይጋለጣሉ። ይህ 'ሲሊኮሲስ' የተባለው የሳንባ ነቀርሳ ከማይድኑ በሽታዎች ይመደባል። በሽታው ከወርቅ ዐለቶች የሚወጣን ብናኝ በትንፋሽ በመሳብ የሚመጣ ነው።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ታዲያ ለነዚህ ታማሚዎችና የሟች ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈል የሚያስገድድ ነው። ይህ ውሳኔ አራት ዐስርታት ከፈጀና እጅግ ከተራዘመ የፍርድ ቤት ሙግት በኋላ መሆኑ ትልቅ ትኩረትን ስቧል።

ከዚህ ወዲህ ለሚከፈቱ ተመሳሳይ የፍርድ ቤት ክሶችም ጥሩ አብነት ሆኖ የተሳለጠ የፍርድ ሂደት እንዲኖር ምክንያት ይሆናልም ተብሏል።

ግዙፎቹ ኩባንያዎች ለታማሚ ወርቅ ቆፋሪዎች በካሳ መልክ ለመክፈል የተስማሙት አምስት ቢሊዮን የደቡብ አፍሪካ ራንድ ነው። ይህ በዶላር ሲሰላ አራት መቶ ሚሊዮን ይደርሳል። የካሳ ተከፋዮቹ በዐስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጉልበት ሠራተኞች ናቸው።

ይህ ረዥም ዓመታትን የወሰደው የፍርድ ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በደቡብ አፍሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መጽደቅ ይጠበቅበታል።

እጅግ ለከፋ የጤና ቀውስ የተጋለጡ የጉልበት ሠራተኞቻቸውን ለመካስ ከተስማሙት የወርቅ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ ሀርመኒ ጎልድ፣ ጎልድ ፊልድስ፣ አፍሪካን ሬይንቦው ሚነራልስ፣ ሲባኒ ስቲል ዎተር፣ አንግሎ ጎልድ አሻንቲ እና አንግሎ አሜሪካን ዋና ዋናዎቹ ናቸው።