ቦይንግ አውሮፕላኖችን በመግዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስራ አንድ ቦይግን 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ ለመግዛት መዋዋሉን አስታውቋል።

አየር መንገዱ እና ቦይንግ ከዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በዱባይ ከተማ ሰኞ ዕለት በተካሄደው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላኖች ኤግዚቢሽን ላይ ነው።

ይህ ስምምነት አየር መንገዱ ቦይንግ አውሮፕላኖችን በመግዛት በአፍሪካ ቀዳሚው አድርጎታል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ጋር ያለው አጋርነቱ እያደገ መሄዱን በወቅቱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ 737፣ በ777 እና በ787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ብዛት ቀዳሚው ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2024 ስምንት 777 እንዲሁም ተጨማሪ 12 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከኩባንያው ጋር ተፈራርሟል።

ከዚህም በተጨማሪ ከሁለት ዓመት በፊት በዚሁ የዱባይ የአውሮፕላን አውደ ርዕይ ላይ በ2023 አየር መንገዱ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ጨምሮ 31 አውሮፕላኖች ለመግዛት ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ጋር ከስምምነት ደርሷል።

አየር መንገዱ ግዢ ለመፈጸም ከስምምነት ላይ የደረሰው ግዙፉን 11 ቦይንግ 787 ድሪምላይነር እንዲሁም 20 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ነው።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስምምነቱ ይፋ በሆነበት ወቅት "ተጨማሪ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ለመግዛት በዱባይ የአውሮፕላን አውደ ርዕይ ላይ ይፋ ስናደርግ ትልቅ ደስታ ይሰመናል" ብለዋል።

"እነዚህ ግዢዎች በራዕያችን እና በስትራቴጂያችን ላይ ያስቀመጥነውን የእድገት ዕቅድ የሚያሳካ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመንገደኞችን ምቾት እና ፍላጎት በመጠበቅ ተመራጭነቱን ለማሳደግ እና ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚረዳው አየር መንገዱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ እና ግዙፍ የሆኑትን 4 ኤር ባስ ኤ350 እና 21 ኤርባስ ኤ350-900ኤክስደብሊውቢን ጨምሮ 160 በላይ ለረዥም እና ለመካከለኛ ርቀት የሚገለገልባቸው አውሮፕላኖች አሉት።

አየር መንገዱ እስካሁን ድረስ ከ60 በላይ አውሮፕላኖችን ለመግዛት አዝዞ ለመረከብ እየተጠባበቀ መሆኑን ድረገፁ ላይ የተቀመጠው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት ቦይንግ አውሮፕላኖች ናቸው።

በርካታ አውሮፕላኖችን ያዘዙ የአፍሪካ አየር መንገዶች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ለመግዛት ባለፉት ዓመታት ትዕዛዝ ሰጥቷል። አየር መንገዱ "ራዕይ 2035" ብሎ በያዘው ዕቅድ ከአስር ዓመታት በኋላ የአውሮፕላኖቹ ቁጥር አሁን ካሉት ከዕጥፍ በላይ ለማድረስ እየሠራ ነው።

በአፍሪካ ትልቁ እና ስኬታማ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአስር ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2035 በዓለም ላይ ካሉ 20 ቀዳሚ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ለመሆን ዕቀድ አለው።

በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አውሮፕላኖችን ከቦይንግ በማዘዝ የሚታወቁት ኳታር እና ኤምሬትስ አየር መንገዶች ሲሆኑ፣ ትኩረታቸው ሰፊ አካል ያላቸው ግዙፍ አውሮፕላኖች ላይ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ታዋቂ ከሆነው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ በርካታ እና ተደጋጋሚ አውሮፕላኖችን ባለፉት ዓመታት በማዘዝ ከአፍሪካ ቀዳሚው እና ተቀናቃኝ የሌለው ነው።

አየር መንገዱ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በረራዎች የሚያገለግሉት ጠበብ ያለ አካል ባላቸው አውሮፕላኖች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ቢሆንም፣ ለግዙፍ አውሮፕላኖችም ፍላጎት አለው።

ከምሥረታው ወዲህ ከግዙፉ የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን እና ከዚህ በፊት ለመግዛት የጠየቃቸው የአውሮፕላኖች ዓይነት እና ቁጥር የሁለቱን ተቋመት ጠንካራ ግንኙነት ያመለክታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትልቅነቱ እና በአትራፊነቱ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ውስጥ ባለው የገበያ ድርሻ ተፎካካሪ የለውም። በተከታታይ ዓመታት ቀዳሚ የአፍሪካ አየር መንገድ የሆነው ተቋሙ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛት እና በማንቀሳቀስ በአህጉሪቱ ውስጥ ተፎካካሪ እንደሌለው መረጃዎች ያሳያሉ።

እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት በአፍሪካ ውስጥ በርካታ አውሮፕላኖችን ለመግዛት በማዘዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳሚውን ቦታ እንደሚይዝ የአቪየሽን እና የአየር ትራንስፖርት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ሳምንት ይፋ ያደረገው የ11 አውሮፕላኖች ግዢ በአፍሪካ ትልቁ ቁጥር ነው። በተጨማሪም ቀደም ባሉት ዓመታት ለቦይንግ ትዕዛዝ የተሰጡ እና በሂደት ላይ ያሉ ሌሎች ተጨማሪ አውሮፕላኖች አሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተከትሎ በርከት ያሉ አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ለመግዛት የጠየቀው የሴኔጋሉ ኤር ሴኔጋል ሲሆን፣ በተወሰነ ቁጥር ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተፎካካሪ የሆኑት የኬንያ እና የግብፅ አየር መንገዶች አውሮፕላኖችን ለመግዛት ጥያቄ ማቅረባቸውን የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ነገር ግን ባለንበት እና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከቦይንግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የተለያየ መጠን ያላቸውን አውሮፕላኖች በማዘዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሌሎቹን የአፍሪካ አየር መንገዶች በሰፊ ርቀት እየመራቸው ይገኛል።