የፔሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲትን ሴት በስራ ጠቅመዋል በሚል ክስ ከስልጣናቸው ለቀቁ

የፔሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አልቤርቶ ኦታሮላ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፔሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አልቤርቶ ኦታሮላ አንዲት ሴት አትራፊ የሆነ የመንግሥት ኮንትራት( ውሎችን) እንድታገኝ ተጽእኗቸውን ለመጠቀም ሞክረዋል በሚል ክስ ከስልጣናቸው ለቀቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግለሰቧ ጋር ያደረጉትን ንግግር የሚያስደምጡ ድምጾችን የፔሩ ቴሌቪዥን ባለፈው ሳምንት አቅርቧል።

የ57 ዓመቱ አልቤርቶ ኦታሮላ ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልሰሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀረበባቸው ክስ ላይ መደበኛ ምርመራም ተጀምሯል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ባቀረበው ፕሮግራም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ25 ዓመቷ ያዚሬ ፒኔዶ ጋር ሲነጋገሩ ይሰማል።

ግለሰቧ በባለፈው ዓመት የመከላከያ ሚኒስቴር የሆኑ ሁለት የስራ ውሎችን በ14 ሺህ ዶላር እንዳገኘች ተዘግቧል።

አልቤርቶ ኦታሮላ እስከ አውሮፓውያኑ 2022 መጨረሻ ድረስ በመከላከያ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

ፕሬዚዳንት ዲና ቦሎዋርቴ ስልጣን መቆጣጠራቸውን ተከትሎም ኦልቤርቶ ኦታሮላ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሾሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግለሰቧ ያላቸውን ፍቅር ሲናዘዙ እንዲሁም የትምህርት እና የስራ ልምዷን የሚያሳይ ማስረጃ (ሲቪ) እንድትልክላቸው ሲጠይቋትም ይሰማሉ።

በጣቢያው የቀረበው የሁለቱ ግለሰቦች ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ድምጽ ሾልኮ ከመውጣቱ በፊት በስብሰባ ላይ አንድ ጊዜ አግኝተዋት እንደነበር ካሉት ጋር የሚቃረን ሆኗል።

ያዚሬ በበኩሏ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አጠር ላለ ጊዜ ግንኙነት እንደነበራት ካናል ኤል ለተባለው የፔሩ ሚዲያ ተናግራለች።

ሁለቱም ግለሰቦች የድምጽ ቅጂዎቹ አልቤርቶ ኦታሮላ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በአውሮፓውያኑ 2021 የተደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቦሉዋርቴ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካናዳ እያደረጉት ከነበረው የስራ ጉብኝት ቀደም ብለው እንዲመለሱ ጠይቀዋቸዋል። እሱንም ተከትሎ የስራ መልቀቂያቸውን አስገብተዋል።

“ሁልጊዜም ከመንግሥታዊ ስልጣን እንድወጣ የሚፈልጉ አካላት ይህንን በመጠቀም ድምጹን ኤዲት አድርገው ስሜን ለማጠልሸት አላመነቱም” ሲሉም በስራ መልቀቂያቸው ላይ ተናግረዋል።

እሳቸውን ለማዋረድ ሴራ ሲጎነጉኑ ነበር ብለው ከከሰሷቸው መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርቲን ቪዝካርራን ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው እንዲህ አይነት “የማታለል ውንጀላዎችን” አጥብቀው እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።