የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ የ100 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቀደላቸው

አቶ በቴ ኡርጌሳ

የፎቶው ባለመብት, ALPHA MEDIA

ላለፉት ሁለት ሳምንታት ገደማ በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ በአንድ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ወሰነላቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ውሳኔውን ያስተላለፈው መርማሪ ፖሊስ የስልክ ምርመራ ውጤት ለማቅረብ ባለመቻሉ መሆኑን የፖለቲከኛው ጠበቃ አቶ ቦና ያዞ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ አቶ በቴ በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደው ዛሬ ረቡዕ የካቲት 27/2016 ዓ.ም. ረፋድ 4፡00 ገደማ ላይ በዋለው ችሎት ነው።

ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት በሰጠው ቀጠሮ መሠረት የመርማሪ ፖሊስን የምርመራ ውጤት ለመስማት ነበር።

ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ከፈረንሳዊው የአፍሪካ ኢንተለጀንስ ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ጋር አንድ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋዜጠኛው ጋር ፍርድ ቤት የቀረቡት የካቲት 14/2016 ዓ.ም. ነበር።

በዚህ ችሎት መርማሪ ፖሊስ “ከፋኖ እና ኦነግ ሸኔ ጋር በመተባባር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለማነሳሳት ሲንቀሳቀሱ ይዣቸዋለሁ” በሚል 14 የምርመራ ቀናትን ጠይቆ ነበር።

ፍርድ ቤቱ ከተጠየቀው የምርመራ ቀናት ውስጥ አምስቱን ፈቅዶ ላለፈው ሐሙስ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። ይሁንና ከቀጠሮው አንድ ቀን አስቀድሞ ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ከእስር ተፍትቶ ከአገር እንዲወጣ ተደርጓል።

አቶ በቴ በአንጻሩ በቀጠሮው ዕለት በችሎት ቀርበው ምርመራው እስኪጠናቀቅ ተጨማሪ አምስት ቀናት እስር ቤት እንዲቆዩ ተወስኖባቸው ነበር።

የቦሌ ምድብ ችሎቱ ተጨማሪ ቀናት የፈቀደው መርማሪ ፖሊስ “ከሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ማስረጃዎች እያገኘን እና የስልክ መረጃዎችም እየተመረመረ ስለሆነ 14 የምርመራ ቀን ይሰጠኝ” በማለቱ እንደሆነ ጠበቃው አቶ ቦና በዕለቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ፍርድ ቤቱም “ለመጨረሻ ጊዜ” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር አምስት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት የፈቀደው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ የምርመራ መዝገቡን እንዲያቀርብ እንደነበር ጠበቃው አስታውሰዋል። በዛሬው ችሎት ላይም መርማሪ ፖሊስ የምርመራ ውጤቱን ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት የአቶ በቴን ስልክ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) እንደሚያስመረምር ገልጾ የነበረው መርማሪ ፖሊስ፤ በዛሬው ችሎት ላይ “የምርመራ ውጤት አልደረሰኝም” ማለቱን አቶ ቦና ተናግረዋል።

“ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ እና ቀሪውን ውጤት ለመጠበቅ በሚል የ14 ቀን ቀጠሮ ጠይቆ ነበር” ሲሉም መርማሪ ፖሊስ ለሦስተኛ ጊዜ ስላቀረበው የተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቃድ ገልጸዋል።

አቶ በቴን ወክለው የቀረቡት ጠበቆች “የምርመራ ውጤቱ የተዛባ [እና] የሕግ ሂደትን ያልተከተለ መሆኑን” በመጥቀስ የመርማሪ ፖሊስን ጥያቄ ተቃውመው መከራከራቸውን አስረድተዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤቱም ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት “ለዛሬ ይቅረብ የተባለው የስልክ ምርመራ ውጤት ባለመቅረቡ” ፖለቲከኛው አቶ በቴ በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና እንዲወጡ መፍቀዱን ጠበቃው አስታውቀዋል።

“[ሂደቱ ዛሬ] ያልቃል የሚል ግምት አለን። [የገንዘብ ዋስትናው] ከተከፈለ በኋላስ ይለቃሉ አይለቁም የሚለውን አብረን የምናው ጉዳይ ነው” ብለዋል።