ለአንድ ሳምንት የታሰረው ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ “በመንግሥት ውሳኔ” ተፈትቶ ከሀገር እንዲወጣ መደረጉን ጠበቃው ተናገሩ

ፈረንሳዊው የአፍሪካ ኢንተለጀንስ ድረ ገጽ ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ

የፎቶው ባለመብት, Indigo Publications

ለአንድ ሳምንት በአዲስ አበባ እስር ላይ የቆየው ፈረንሳዊው የ “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ፤ “በመንግሥት ውሳኔ” ተፈትተቶ ከሀገር እንዲወጣ መደረጉን ጠበቃው ለቢቢሲ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋዜጠኛው እንደሚፈታ እና ከሀገር የሚወጣበት የአውሮፕላን ቲኬት እንዲዘጋጅ አስቀድመው ለፈረንሳይ ኤምባሲ ማሳወቃቸው ተነግሯል።

ጋዜጠኛው “ከፋኖ እና ኦነግ ሸኔ [የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት] ጋር በመተባባር ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት በመንቀሳቀስም” በሚል ነበር የካቲት 14/ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር የዋለው።

አፍሪካ ህብረት ጉባኤን ለመዘገብ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ፤ ከእስር የተለቀቀው ትናንት ሐሙስ የካቲት 21፤ 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የጋዜጠኛው ጠበቃ ተናግረዋል።

ጠበቃው እንደሚያስረዱት ጋዜጠኛው ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ የፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም፤ ትናንት ሌሊት ስድስት ሰዓት ገደማ ላይ ከኢትዮጵያ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ እንዲበር ተደርጓል።

የጋዜጠኛውን መታሰርን ተከትሎ የፈረንሳይ ኢምባሲ ጉዳዩን “በከፍተኛ ኃላፊዎች” ደረጃ ይዞት እንደነበር የሚናገሩት ጠበቃው፤ ትናንት ጥዋት የመንግሥት አካላት ጋዜጠኛው “እንደሚፈታ እና ትኬቱን እንዲዘጋጅለት” ለኤምባሲው ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

“የኤምባሲው ሰዎች የታሰረበት ቦታ ሄደው [ጋዜጠኛውን] ወደ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ ወስደዋል። እስከ ሁለት ሰዓት አካባቢ ከቆየ በኋላ ወደ ኤርፖርት የሄደው በኢምባሲው ታጅቦ ነው” ሲሉ ጋዜጠኛው ከሀገር የወጣበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

ይሁንና በመንግስት እንዲፈታ ቢደረግም በትኛው አካል በምን አግባብ ውሳኔው እንደተላለፈ መናገር እንደማይችሉ ጠበቃው ጠቅሰዋል።

ጠበቃው፤ የ“ምርመራ መዝገብ ተቋርጧል የሚባለው ግልጽ በሆነ ሁኔታ ‘በግለሰቡ ላይ የተጀመረው የምርመራ መዝገቡ በዚህ ምክንያት ተቋርጧል’ ተብሎ በመዝገቡ ላይ ሲስፍር ነው። ግን ግለሰቡ የተጀመረበት የምርመራ መዝገብ ቢኖርም በመንግስት ውሳኔ ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል” ብለዋል።

በፓሪስ መቀመጫውን ላደረገው አፍሪካ ኢንተለጀንስ ጋዜጠኛ የሆነው አንቷን ትናንት የካቲት 21/ 2016 ዓ.ም ከእስር ተፈትቶ ወደ ፈረንሳይ መመለሱንም ሲፒጄ ከድረገጹ አሳታሚ ኩንቲን ቦትቦል ያገኘውን መረጃ ዋቢ አድርጎም አስፍሯል።

“ጋዜጠኛው እንዲፈታ የጣሩ ሁሉንም ግለሰቦች እና ተቋማትን እናመሰግናለን” ያሉት ቦትቦል “በአገሪቱ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ተፈትተው ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን።" ማለታቸው በሲፒጄ መግለጫ ሰፍሯል።

ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር የዋለውም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ የፖለቲካ ኦፊሰር የሆኑትን አቶ በቴ ኡርጌሳንም ቃለ መጠይቅ እያደረገ በነረበት ወቅት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከጋዜጠኛው በተጨማሪም ፖለቲከኛው አቶ በቴ “ሲቪል በለበሱ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት አባላት” በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ቢቢሲ ስማቸው እንዳይጠቀስ ከጠየቁ የጋዜጣኛው ጠበቃ ሰምቷል።

ፖለቲከኛው እና ጋዜጠኛው የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ቀርበው የነበረ ሲሆን ፖሊስ መረጃዎቹን አጠናቅሮ ለዛሬ የካቲት 22/ 2016 ዓ.ም እንዲቀርቡም ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር።

ፍርድ ቤት ቀርበው በነበረበትም ዕለት ፖሊስ “ከፋኖ እና ከኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ ይዣቸዋለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ መናገሩን ጋዜጠኛውን ወክለው በፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ጠበቃ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ከሰሞኑ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ ጋዜጠኛው ለ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ዘገባ ሽፋን ለመስጠት ፍቃድ አግኝቶ ቢመጣም “ግለሰቡ የጋዜጠኝነት ሙያውን ሽፋን አድርጎ ከመጣበት ዓላማ ፍጹም ተቃራኒ እና ውጭ የሆኑ ተግባራትን ሲያከናውን ነበር” ብለዋል።

ፍቃድ ካገኘበት ውጭ “የኢትዮጵያን የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ሲሞክር፤ በዚህም ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን እና አባላቶችን፣ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን ሲያነጋግር እና መረጃዎችን ሲያሰባስብ ነበር” ብለዋል።

ማንኛውም ጋዜጠኛ ከመጣበት ዓላማ ውጭ መስራት “ህገወጥ ነው” ሲሉም አክለዋል።

የአፍሪካ ኢንተለጀንስ አሳታሚ ጋዜጠኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔን ለመሸፈን ለአንድ ሳምንት እንዲሁም በቀጣዩ ሳምንት ከመሪዎቹ ጉባዔ እና ከኢትዮጵያ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ “ፖለቲከኞች እና ዲፕሎማቶችን” ለማናገር ይችል ዘንድ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የ14 ቀናት ፍቃድ እንዲሰጠው ጥር 16/ 2016 ዓ.ም ደብዳቤ መላኩን ሲፒጄ ተመልክቻለሁ ብሏል።

አንቷን በኢትዮጵያ ለመስራት የሁለት ሳምንት ፈቃድ እንዳገኘም ሲፒጄ ጋዜጠኛው በአየር ማረፊያ የሞላውን ቅጽ መገምገሙን አመልክቷል።

ስምንት ጋዜጠኞችን አስራ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራትም ለጋዜጠኞች አስከፊ በመሆን ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ሲፒጄ በ2023 ባደረገው ሪፖርት አስፍሯል።

ከነዚህ ውስጥ ግማሾቹ የታሰሩት ከአማራ ክልል ጋር በተቀሰቀው ግጭት ጋር ተያይዞ በተጣለው አስቸኳይ አዋጅንም ተከትሎ ነው።