የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ አምስት የምርመራ ቀናት በፍርድ ቤት ተፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Reporter
“ሸኔ እና ፋኖን በማስተባበር በአዲስ አበባ ሁከት ለመፍጠር” በመንቀሳቀስ የተጠረጠሩት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ የአምስት ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ተፈቀደ።
የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው ዛሬ አርብ የካቲት 22፤ 2016 ዓ.ም. የዋለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ነው።
አቶ በቴ ከፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ጋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 14፤ 2016 ዓ.ም. ነበር።
ከአቶ በቴ ጋር በቁጥጥር ስር የዋለው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ትናንት ዕኩለ ሌሊት ላይ “በመንግሥት ውሳኔ” ከእስር ተፈትቶ ከሀገር መውጣቱን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰሩ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ቃለ መጠየቅ ሲያደርግላቸው የነበረው ጋዜጠኛ ከእስር ቢፈታም አቶ በቴ ግን ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንደተፈቀደባቸው ጠበቃቸው አቶ ቦና ያዞ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ በቴ እና ጋዜጠኛ አንቷን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ ሆነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።
ፖሊስ በባለፈው የችሎት ውሎ፤ “ከፋኖ እና ኦነግ ሸኔ ጋር በመተባባር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለማነሳሳት ሲንቀሳቀሱ ይዣቸዋለሁ” በሚል 14 የምርመራ ቀናትን ጠይቆ ነበር።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጠየቀው የምርመራ ቀናት ውስጥ ስድስቱን ብቻ ፈቅዶ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ጋዜጠኛ አንቷን ትናንት ዕኩለ ሌሊት ከእስር መፈታቱን ተከትሎ በዛሬው የችሎት ውሎ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ በቴ ኡርጌሳ ብቻ ናቸው።
ፖሊስ በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ፤ “ሸኔን እና ፋኖን በማስተባበር አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት ለመፍጠር ጋዜጠኛው ደግሞ እንዴት ሽፋን እንደሚሰጥ ስትራቴጂ አውጥተዋል ይሄ እጃችን ገብቷል” ማለቱን ጠበቃ ቦና ተናግረዋል።
ፖሊስ ባለፉት ስድስት ቀናት የአቶ በቴን ስልክ ለማስመርመር ለኢንፎርሜሽነ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) መላኩን፥ የተጠርጣሪውን አሻራ መቀበሉን ለችሎቱ አስረድቷል።
ፖሊስ አክሎም፤ “ከሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ማስረጃዎች እያገኘን ስለሆነ የስልክ መረጃዎችም እየተመረመረ ስለሆነ 14 የምርመራ ቀን ይሰጠኝ” ሲል መጠየቁን ጠበቃው ተናግረዋል።
የአቶ በቴ ጠበቃ በበኩላቸው “ዋና ወንጀል አድርጊ የተባለው ተለቅቋል። እሱ በተለቀቀበት ሁኔታ ደግሞ [በቴ ኡርጌሳ ላይ] አዲስ ወንጀል እየተፈለገ [ነው] ይሄ አግባብ አይደለም” የሚል መከራከሪያ ማቅረባቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የስልክ ምርመራን በተመለከተም፤ “ስልኩ በእሱ [በአቶ በቴ] እጅ አይደለም ፖሊስ ጋር ነው። ያለውን ማስረጃ ማጥፋት አይችልም በዚህ ምክንያት የዋስትና መብት ሊከለከል አይገባም” ሲሉ ተከራክረዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፤ የስልክ ምርመራን በተመለከተ ፖሊስ ያነሳውን ሃሳብ በመቀበል “ከማስጠንቀቂያ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ” አምስት የምርመራ ቀናትን መፍቀዱን ጠበቃ ቦና ለቢቢሲ ተናግረዋል።












