ቦይንግ ላይ የደህንነት ስጋቱን የገለጸው መካኒክ ከስራ ተባረርኩ አለ

ቦይንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቦይንግ አውሮፕላኖችን የሚጠግን ግለሰብ ከአውሮፕላኑ የደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ስጋቱን በመግለጡ ከስራ መባረሩን አስታወቀ።

ግለሰቡ “ወሬ አቀባይ” በሚልም ከስራው መቀነሱን የገለጸው።

በቦይንግ 787 አውሮፕላኖች ወሳኝ ክፍል ላይ ደረጃውን ያልጠበቀ የማምረቻ እና የጥገና ሥራ መመልከቱን ሪቻርድ ኩውቫስ ተናግሯል።

የደህንነት ሥራው ጥብቅ ክትትል ይደረግበታል ወይ በሚል ጥያቄዎች እየተነሱበት የሚገኘው ቦይንግ ጉዳዮቹ መመርመራቸውን እና “የደህንነት ስጋት አለማቅረቡን” ገልጿል።

ኩውቫስን የሚወክሉ ጠበቆች በበኩላቸው ከባድ የህዝብ ደህንነት ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ሪፖርት እንዳደረገ እና ለፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር እና ለሥራ ጤና እና ደህንነት አስተዳደር ቅሬታ ማቅረቡን አክለዋል።

በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ለ40 ዓመታት ያገለገለው ኩውቫስ ለስፕሪት ኤሮሲስተምስ ተቀጥሮ በቦይንግ 787 የፊት አካላት ላይ ይሠራ ነበር።

“ደረጃውን ያልጠበቀውን ሥራ ለይቶ ስጋቱን ገልጿል። ስፕሪት እና ቦይንግ ግን ችግር ያለባቸውን የምርት ሂደቶችን ማስቆም አልቻሉም” ብለዋል የኩውቫስ ተጠበቆች።

በቀረቡ ሕጋዊ ሰነዶች መሠረት አንድ የሥራ ባልደረባው “በመካከላችን አቃጣሪ አለ” ሲል ተናግሯል።

ኩውቫስ መጋቢት 2024 በስፕሪት ኤሮሲስተምስ ከሥራው እንደተባረረ ተናግሯል።

“ከደህንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በቁም ነገር ስለምንወስድ የአንድ ንዑስ ተቋራጭ ሠራተኛ ያቀረበውን ስጋት በጥልቀት አጣርተናል” ሲል ቦይንግ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

የተነሱት ጉዳዮች የደህንነት ስጋት እንዳልሆኑ በመረጋገጡና ምላሽ መሰጠቱን ቦይንግ ተናግሯል።

የስፕሪት ኤሮሲስተምስ ቃል አቀባይ ጆ ቡቺኖ በበኩላቸው ኩባንያው “ጉዳዩን እየተመለከተው ነው” ብለዋል።

"ሁሉም ስጋት ያለባቸው የስፕሪት ሠራተኞች ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በማወቅ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ እናበረታታለን" ብሏል።

የኩውቫስ ጠበቆች የሆኑት ዴብራ ካትዝ እና ሊዛ ባንክስ ከዚህ ቀደም የቦይንግን መረጃ ያጋለጠውን ሳም ሳልፉርን ወክለው ነበር። ሳልፉር በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ ኮንግረስ ቀርበው ቦይንግ የጥራት ችግር አለበት ብሎ በመናገሩ እንግልት እና ዛቻ እንደደረሰበት ተናግሯል።

የሳልፉር ስጋትም ከቦይንግ 787 ሞዴልን ምርት ጋር የተያያዘ ነበር።

በጥር ወር በበረራ ላይ እያለ በሩ ከተገነጠለው የቦይንግ 737 ማክስ የተለየ ሞዴል ነው።

ይህ ክስተት የቦይንግን የደህንነት ደረጃዎች የበለጠ እንዲመረመሩ አድርጓል።

በሚያዝያ ወር ቦይንግ ምንም ዓይነት የበቀል እርምጃ እንደማይወስድ ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ ስጋታቸውን የሚገልጹ ሠራተኞች ጭማሪ ማሳየቱን ተናግሯል።

ቦይንግ ወደ “ጠንካራ የሪፖርት አቀራረብ ባህል” እድገት መኬዱን ያሳያል ብሏል።

"ደህንነትን እና ጥራትን ከሁሉም በላይ በማስቀደም መረጃዎችንን ለተቆጣጣሪዎቻችን፣ ደንበኞቻችን እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በግልጽ እናካፍላለን" ብሏል።