በፓኪስታን በሙቀት ወላፈን ምክንያት በቀናት ውስጥ ከ500 በላይ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፓኪስታን ከፍተኛ በሆነው የሙቀት ወላፈን ምክንያት በስድስት ቀናት ውስጥ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
ደቡባዊ ፓኪስታን በመታት የሙቀት ወላፈን ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር የጨመረ ሲሆን ኢዲሂ የተሰኘው የአምቡላንስ አገልግሎት በየቀኑ ከ30 እስከ 40 የሞቱ ሰዎችን በካራቺ በሚገኘው የአስከሬን ማስቀመጫ ክፍል እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል።
ባለፉት ስድስት ቀናት ውስጥ 568 አስከሬኖችን የሰበሰበ ሲሆን 141 ያህሉ ማክሰኞ ዕለት እንደሆነ ገልጿል።
የእያንዳንዱ ሰው ሞት መንስዔ ምን እንደሆነ በትክክል ለመናገር ገና ነው ቢባልም ሞቶቹ የተከሰቱት በካራቺ ከተማ ያለው ሙቀት በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረበት ወቅት ነው።
በግዛቲቷ ያለው የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሲሆን ያዘለው ከፍተኛ ወላፈን ተጨምሮበት 49 ዲግሪሴንቲግሬድ መጠን ያለው ሙቀት መሰማቱን ሪፖርቶች ጠቁመዋል።
በርካቶችም እርዳታ ለማግኘት ወደ ሆስፒታሎች አቅንተዋል።
የካራቺ ሲቪል ሆስፒታል በባለፈው ሳምንት እሁድ እና ረቡዕ መካከል በከፍተኛ የሙቀት ወላፈን ምክንያት 267 ሰዎች እንደመጡ የሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ኢምራን ሳርዋር ሼክ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 12 ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።
“ወደ ሆስፒታሉ የመጡ በአርባዎቹ እና በ20ዎቹ እድሜ የነበሩ ቢሆንም አብዛኞቹ በ60ዎቹ እና 70ዎቹ ዕድሜ ላይ ያሉ ናቸው። “ ሲሉ ዶክተር ኢምራን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ ከፍተኛ ትኩሳትን ጨምሮ ማስታወክ፣ ተቅማጥ የመሳሳሉ ምልክቶች ታይተውባቸዋል ተብሏል።
“በውጭ ስራቸውን እያከናወኑ ያሉ ሰዎችን ይህንን ከፍተኛ የሙቀት መጠን ለመቋቋም ውሃ አብዝተው እንዲጠጡ እና ቀለል ያሉ ልብሶችን እንዲለብሱ ነግረናቸዋል” ብለዋል።
በአንድ የሜትሮሎጂ ባለሙያ “ከፊል የሙቀት ወላፈን” መሆኑ የተገለጸው ከፍተኛ የሙቀት መጠን የተከሰተው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው።
ለህዝቡ እፎይታ ለመስጠት የሚሞክሩ ማዕከሎች እና ካምፖች ተዘጋጅተዋል።
ህጻናት ራሳቸው ለማቀዝቀዝ በፋፏቴዎች እየተነከሩ ሲጫወቱ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
“ልብሴ በሙሉ በላብ ረጥቧል። ተመልከተኝ” ሰሉሉ ራሳቸውን ለማቀዝቀዝ እየሞከሩ የነበሩት መሃመድ ኢምራን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።












