በጣልያን ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚገጥማቸው ፈተና ምንድን ነው? ለምንስ ዘግይተው ይመረቃሉ?

የምረቃ ቆብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አውሮፓዊቷ አገር ጣልያን የበርካታ አፍሪካውያን የትምህርት መዳረሻ ናት።

እንደ ዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት መረጃ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2021 በጣልያን፣ 72 ሺህ 284 አፍሪካውያን ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ነበር።

ከእነዚህ መካከል 414ቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ 73ቱ ደግሞ ኤርትራውያን ናቸው። እነዚህ ተማሪዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ እና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ናቸው።

በጣልያን ፒሳ ከተማ የምትገኘው ሳንታና ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው ዓመት በተለያየ የትምህርት ዓመት ላይ የሚገኙ 11 ኢትዮጵያውያን የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያስተማረች ነው።

አሃዞቹ እንደሚያመለክቱት የትምህርት ዕድል አግኝተው የውጭ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚቀላቀሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቁጥር ጥቂት ሲሆኑ፣ በተያዘለት ጊዜ አጠናቀው የሚመረቁትም ያን ያህል ናቸው።

ሦስት ዓመት የሚወስደውን ትምህርት በአራት እና በአምስት ዓመት የሚያጠናቅቁ፣ በአራት ዓመት የሚጠናቀቀው የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራምም እስከ ስምንት ዓመት ድረስ የሚወስድባቸው እንዳሉ ቢቢሲ ካነጋገራቸው መምህራን እና ተማሪዎች መረዳት ችሏል።

ለመሆኑ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ለምን በተቀመጠው የትምህርት ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር መሠረት አይመረቁም?

ቢቢሲ ተማሪዎችን እና መምህራንን በማነጋገር አምስት ዐበይት ምክንያቶችን ነቅሶ ለማውጣት ሞክሯል።

የትምህርት ሥርዓት መለያየት

ዮናስ ሰይፉ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ አውሮፓዊቷ አገር ጣልያን ካቀና ዓመታት ተቆጥረዋል። ሁለተኛ ዲግሪውንም ሦስተኛ ዲግሪውንም በዚያው ነው ያጠናቀቀው።

አሁን ላይ በሳንታና ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሮኒክስ ምህንድስና በረዳት ፕሮፌሰርነት ላለፉት አራት ዓመታት እየሠራ ይገኛል። ከማስተማር ባሻገርም ጥናት እና ምርምር እየሠሩ ያሉ ተማሪዎችን ይከታተላል።

ዮናስ አዳዲስ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚቀላቀሉ ተማሪዎችን በማገዝም ይታወቃል።በዩኒቨርሲቲው ባለው ቆይታ እና ከተማሪዎች ጋር ባለው ግንኙነት ተማሪዎች ዘግይተው የሚመረቁበትን ምክንያቶች ለመታዘብ ችሏል።

እርሱ እንደሚለው ምክንያቶቹ የተለያዩ ናቸው።እንደ የትምህርት ደረጃውም ይለያያል።

ሁሉንም ወደ አንድ የሚያመጣው ምክንያት ግን በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ሥርዓት በጣልያን ካለው ጋር መለያየቱ ነው።

በአውሮፓ ትምህርት በጊዜ ማነቆ የተጨናነቀ አይደለም።

ተማሪዎች ማሟላት ያለባቸውን ‘ክሬዲት አወር’ [የትምህርት ጊዜ] ካሟሉ ለፈተና ዝግጁ በሚሆኑበት ወቅት መፈተን እና ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ የሚችሉበት ዕድል አለ። ይህም በተመሳሳይ የትምህርት ሥርዓት ያላለፉ ተማሪዎችን እንዲዘናጉ እንደሚያደረግ ዮናስ ይናገራል።

ዮናስ ሰይፉ፣ ሊዮናርዶ ካፕሮኒ እና ቢኒያም መኮንን

የፎቶው ባለመብት, Yonas/Leonardo/ Biniam

የምስሉ መግለጫ, ረዳት ፕሮፌሰር ዮናስ ሰይፉ፣ረዳት ፕሮፌሰር ሊዮናርዶ ካፕሮኒ እና ቢኒያም መኮንን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሳቢያንሳ ዩኒቨርሲቲ የኢንተርናሽናል ሂውማኒቲስ የመጀመሪያ ዲግሪ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ረድኤት ሌንጮም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያላት።

ረድኤት እንደምትለው የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በአጠቃላይ 180 ክሬዲት አዎር፣ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ደግሞ 120 ‘ክሬዲት አዎር’ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።አብዛኞቹ የሚጠይቁትም የዓመቱን ግማሽ እንዲያሟሉ ነው።

ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመቀጠል በዓመት ከሚወሰደው ግማሹን ማጠናቀቅ ከቻሉ ፈተናቸውን በመረጡት ጊዜ መውሰድ ይችላሉ።

“የመጀመሪያውን ወሰነ ትምህርት ፈተና ጥር እና የካቲት ወይም ሐምሌ እና ነሐሴ መውሰድ ይቻላል። ስለዚህ ከሁለቱ በአንዱ መርጬ መፈተን እንደምችል ስለማውቅ እንድሳነፍ ያደርገኛል። ምክንያቱም በመጀመሪያው ፈተና ብወድቅ ድጋሚ ልፈተን እችላለሁ” ስትልም ያሉትን አማራጮች ታስረዳለች።

ነገር ግን ከመጀመሪያው የባሰ ውጤት ሊመጣ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል።

ይህም በቀጣይ በሚኖሩት የትምህርት ዓመታት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ትምህርትን በጊዜ ካለማጠናቀቅ ባሻገር የትምህርት ዕድልን እስከመነጠቅ ሊያደርስ እንደሚችል ረድኤት ትናገራለች።

የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችም የሚጠበቅባቸውን ክሬዲት አዎር እና ጥናታዊ ጽሑፍ ሕትመት ካሟሉ መመረቂያ ጽሑፋቸው ዝግጁ በሚሆኑበት ወቅት ማቅረብ የሚችሉበት ዕድል አለ።

ረዳት ፕሮፌሰር ዮናስ እንደሚለው እነዚህ በትምህርት ሥርዓቱ ያሉ ልዩነቶች በአንድ በኩል ተማሪዎቹ እንዳይጨናነቁ ቢያደርግም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያዘናጋል።

“የጣልያን የትምህርት ሥርዓት ከታች ጀምሮ በጥረት የተሞላ ነው። ጠንክሮ የመሥራት ባህል አለ” የሚለው ዮናስ፣ ይህ ዘና ያለ የትምህርት ሥርዓት ታዲያ ጠንክሮ በመሥራት ውስጥ አልፈው ያልመጡትን ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ሲያዘናጋ እና ለተደራራቢ ችግር ሲዳርግ እንደሚታይ ይናገራል።

በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ነገ ዛሬ ሲሉ ወይም መስጠት ያለባቸውን ትኩረት ባለመስጠት በአራት ዓመታት የሚጠናቀቀውን የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመጨረስ እስከ ስምንት ዓመት ሊወስድባቸው ይችላል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በመቀለ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሲሠራ የቆየው እና በሳንታና ዩኒቨርሲቲ በሂውማን ስተዲስ እና ግሎባል ፖሊቲክስ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነው ቢኒያም መኮንንም ይህንኑ ሃሳብ ነው የሚጋራው።

ቢኒያም በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ ማሻሻያ ማድረግ ወደፊት የሚመጡት ተማሪዎች ከዓለም አቀፍ የትምህርት ሥርዓት ጋር በቀላሉ እንዲተዋወቁ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ያነሳል።

ይህም በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ዕድል በቀላሉ እንዲያገኙ እና ዕድሉን ካገኙ በኋላም ህልማቸውን ለማሳካት ይረዳቸዋል ይላል።

የሳንታና ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ

የፎቶው ባለመብት, Scuola Superiore Sant'Anna FB

የምስሉ መግለጫ, የሳንታና ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ

የሚያገኙት የትምህርት ዕድል ዓይነት

በኢትዮጵያ ነጻ የትምህርት ዕድል ለማግኘት በበይነ መረብ የሚፈልጉ ተማሪዎች ስለሚሰጣቸው ዕድል በቂ እውቀት የላቸውም።

ነጻ የትምህርት ዕድል ሲባል ሁሉም ወጪያቸው የሚሸፈንላቸው ይመስላቸዋል። በኢኮኖሚ ወዳደጉት አሜሪካ እና አውሮፓ አገራት ለመሄድ ሲታሰብም የተደላደሉ ነገሮችን የመጠበቅ ልማድ አለ።

ሆኖም አንዳንዶች የነጻ ትምህርት ዕድል ያገኛሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሙሉ የትምህርት ዕድል ማለትም የመኖሪያ እና የትምህርታቸው ወጪ የሚሸፈንበት ዕድል ይሰጣቸዋል።

የትምህርት ዕድሉን እንደሚሰጣቸው ተቋም አቅምም የሚመደብላቸው በጀት በቂ የማይሆንበት አጋጣሚ አለ።

በመሆኑም ተማሪዎች በዚህ ላይ በቂ እውቀት ሳይኖራቸው ወደ አውሮፓ ተሻግረው ትምህርት ከጀመሩ በኋላ ፈተና ይገጥማቸዋል።

የግል ስፖንሰር እንዳላቸው የሐሰት መረጃ በማቅረብ የትምህርት ዕድሉን ብቻ ካገኙ በኋላ የግል ወጪያቸውን የሚሸፍንላቸው አጥተው ያለ ደጋፊ የሚቀሩም ጥቂት አይደሉም።

በመሆኑም የኑሮ ጎዶሏቸውን ለመሙላት ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሥራ መሥራት የግድ ይሆንባቸዋል።

እነዚህ ውጣ ውረዶችም ተማሪዎቹ ለትምህርታቸው ተገቢውን ትኩረት እንዳይሰጡ እና በተያዘው ጊዜ እንዳያጠናቅቁ ወደ ኋላ ይጎትታቸዋል። ባስ ሲልም ለመኖሪያ ቤት የሚከፍሉት አጥተው ጎዳና ላይ የሚወድቁ እንዲሁም ከዓላማቸው ተደናቅፈው ሌላ የሕይወት ዳገት የሚገፉ እንዳሉ ተማሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የባህል፣ የቋንቋ እና የዘር ልዩነት

ተማሪዎች ከሚያውቁት የባህል፣ የቋንቋ እና የአኗኗር ዘይቤ ሲወጡ የሚደርስባቸው ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጫናም ቀላል አይደለም።

የከፍተኛ ትምህርት የማስተማሪያ ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ከሆኑ አገራት ወደ ጣልያን የሚያቀኑ ተማሪዎች ከጣልያን ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ጋር ራሳቸውን ለማላመድ ጊዜ ይወስድባቸዋል።

መኖሪያ ቤት መከራየት፣ከአገሬው አኗኗር እና ምግብ ጋር መላመድ የራሱ የሆነ ተግዳሮት አለው።

በተማሪ የገንዘብ አቅም የሚከራየው ቤት ማግኘት ትልቅ ተግዳሮት ሆኖበት እንደነበር የሚያስታውሰው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ፣ በቀጥታም ባይሆን የዘር መድልዎ ይደረግባቸው እንደነበር ይናገራል።

“ቤት የምንፈልገው በኦንላይን ነው። ፕሮፋይላችን አፍሪካዊ እና ጥቁር መሆናችንን ሲያውቁ ቤታቸውን ላለማከራየት ሌላ ምክንያት ይሰጡናል፤ በዚህም ምክንያት ሦስት ወር እና አራት ወር መጠባበቅ የግድ ይላል” ይላል።

አንዳንዶች የሚከራዩት ቤት እስከሚያገኙ ድረስ ከሚያገኙት ከፍተኛ የሆነውን በወር 500 ዩሮ [32 ሺህ ብር] እየከፈሉ ሆስቴል ውስጥ ለመቆየት እንደሚገደዱ ይናገራል።

ተጨማሪ ሥራ ለመሥራትም የሥራ ፈቃድ ስለሚያስፈልግ ራስን መደጎም አይቻልም። የሥራ ፈቃዱን ቢያገኙ እንኳን ጣልያንኛ ቋንቋ ስለማያውቁ ሥራ ማግኘቱ ቀላል አይደለም።

በመሆኑም ከባህል፣ ከቋንቋ እና ከአስተዳደራዊ ሥርዓቶች ጋር ራሳቸውን ለማላመድ የሚወስድባቸው ጊዜ በትምህርታቸው ላይ ጫና ያሳድራል።

የተዘረጋ የቤተሰብ እጅ

ይህ ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚያጋጥም ፈተና ነው።አገር ቤት ያለ ቤተሰብ ውጭ ካለ የቤተሰብ አባሉ ድጎማ እና እርዳታ ይጠብቃል።

አውሮፓ እና አሜሪካ ማለት ገንዘብ የሚታፈስበት እና የድሎት ሕይወት የሚኖርበት አድርገው የሚቆጥሩ በርካቶች ናቸው።

ትዕዛዞች ይበረክታሉ፤ ኃላፊነት ይጨምራል። በገንዘብ ቤተሰብን መደጎም የሚጠበቅ እና ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ማኅበራዊ ልማድ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አስገዳጅ ነው።

ይህንንም ፍላጎት ለማሟላት ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን እንቅልፋቸውን እና እረፍታቸውን መስዋዕት አድርገው ራሳቸውን ባገኙት ሥራ ይጠምዳሉ። ይህም በትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሌላኛው ምክንያት ነው።

ከዚህም ባሻገር ከተመረቁ በኋላ ማረፊያቸው የሚያሳስባቸውም ተማሪዎች አሉ። በአገራቸው የተሻለ የሥራ ዕድል አለመኖርና የሰላም እጦት ቶሎ ተመርቆ ለመሄድ ያላቸውን ፍላጎት ሲቀንሰውም ይስተዋላል።

በመሆኑም የተሻለ ሥራ እስከሚያገኙ እና እስከሚያመቻቹ ድረስ የትምህርት ሥርዓቱ የሰጠውን ዕድል በመጠቀም የትምህርታቸውን ጊዜ ለማራዘም ይገደዳሉ።

የተቋማት ቢሮክራሲ

አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝተው ለመሄድ ሲነሱ የሚገጥማቸው ፈተና የሚጀምረው በገዛ አገራቸው ነው።

የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን እና የድጋፍ ደብዳቤዎችን ለማጻፍ በየተቋማቱ ያለው ቢሮክራሲ ቀላል እንዳልሆነ ተማሪዎች ይገልጻሉ።

ይህ በእጃቸው ከገባ በኋላም ቪዛ ማግኘት አዳጋች ነው። ኢትዮጵያውያኑ በአገሪቷ ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት በዚያው ወጥተው ይቀራሉ በሚል ግምት ቪዛ ይከለከላሉ።

በእነዚህ እና መሰል ምክንያቶች ከተቀመጠው የትምህርት የጊዜ ሰሌዳ እንዲዘገዩ ይሆናል።

በቅርቡም የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያውያን ላይ የቪዛ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።

ኅብረቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ በአውሮፓ አገራት የሚኖሩ ዜጎቹን መልሶ ለመቀበል ያሳየው ተባባሪነት አናሳ ነው ሲል የጣለው የቪዛ ገደብ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ጊዜ በላይ ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ገብተው መውጣት የሚችሉበት ቪዛ (multiple entry) ማግኘት እንዳይችሉ ይከለክላል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ቪዛ ለማግኘት የሚጠብቁት ጊዜ ከ15 የሥራ ቀናት ወደ 45 የሥራ ቀናት ከፍ እንዲል ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህም በተማሪዎች ላይ ከዚህ ቀደሙ በባሰ ሁኔታ ተፅዕኖ ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ተማሪዎቹ ጣልያን ከደረሱ በኋላም አስፈላጊ የመቆያ ፈቃድ እና ሌሎች ሰነዶች ቶሎ ስለማይሟሉላቸው ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ሳይለቀቅላቸው እንደሚቆዩ ረድኤት ትናገራለች።

“ከኢትዮጵያ ገንዘብ ይዞ መምጣት አቅም አይፈቅድም። ቢኖርም እንኳን ትንሽ ዩሮ ነው የሚሰጡት። በመሆኑም ከመጣን በኋላ ሥራ መሥራት የግድ ነው” የምትለው ረድኤት፣ በዚህ ሁኔታ ትምህርትን ተረጋግቶ መማር ፈታኝ መሆኑን ትገልጻለች።

በጣልያን የመቆያ ፈቃድ ለማግኘት እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ እንደሚወስድ የሚገልጸው ተማሪም፣ ይህም በተለይ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ወደ ሌሎች አገራት ተጉዘው ስብሰባዎች፣ ጉባኤዎች እና ወቅታዊ ትምህርቶች ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚያደርጋቸው ያስረዳል።

የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመቀጠል ማሟላት ካለባቸው 'ክሬዲት አዎሮች' በተጨማሪ ጉባኤዎች እና ስብሰባዎች ላይ መሳተፍ እና አጫጭር ትምህርቶችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህም ባሻገር የዩኒቨርሲቲዎች ቢሮክራሲ እና አማካሪዎች ከተማሪዎች ጋር ያላቸው ተግባቦት ለተማሪዎች ዘግይቶ መመረቅ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።

በሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት በምትሰጠው የጣልያኗ ሳንታና ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ቢቢሲ ያነጋገራቸው መምህራን እና ተማሪዎች ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው በእፅዋት ዘረመል (ፕላንት ጀኔቲክስ) መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሊዮናርዶ ካፕሮኒ በጣልያን ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ያለው ችግር የቢሮክራሲ እንደሆነ ከተማሪዎቻቸው እንደሰሙ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ሲመረቁ ጭንቅላታቸው ላይ የሚያደርጉት የወይራ ቅጠል አክሊል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተማሪዎች ሲመረቁ ጭንቅላታቸው ላይ የሚያደርጉት የወይራ ቅጠል አክሊል

ሊዮናርዶ እንደሚሉት ተማሪዎች ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ለማቅረብና በአማካሪዎች እና በፈታኞች መካከል በሚኖረው ቢሮክራሲ ምክንያት ይዘገያሉ።

በዚህም ምክንያት ሳንታና ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት ባለፈው ዓመት በአስተዳደር ውስጥ ማሻሻያዎችን እንዳደረገች ጠቅሰዋል።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ይህ ችግር የሚያጋጥመው በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ላይ ጭምር ነው።

“ስለ የትምህርት ሥርዓቱ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው አንዳንድ ተማሪዎችም አሉ” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ትምህርታቸውን የሚጨርሱበት ጊዜ በተራዘመ ቁጥር የገንዘብ ድጋፍ በማጣት ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚቸገሩ እንዳሉም አንስተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱን እና የአፍሪካውያን ተማሪዎችን ፍላጎት ያገናዘበ በቂ የገንዘብ ድጋፍ አለመኖሩ የተማሪዎችን ሕይወት ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።

ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በኋላ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ አጋጥሟል። ሆኖም አሁንም ለተማሪዎች የሚመደበው በጀት በቂ አለመሆኑን ተማሪዎቹ እና መምህራኑ ተናግረዋል።

ግራጫ መስመር

በርካታ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች እና ቱሪስቶች በሚርመሰመሱባት የጋሊሊዮ ጋሊሊ ከተማ ፒሳ የምትገኘው ሳንታና ዩኒቨርሲቲ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን አፍርታለች።

እነዚህ ምሁራን በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ አገራት በሚገኙ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው በኃላፊነት ደረጃ እየሠሩ ይገኛሉ።

በአውሮፓ በሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም በመምህርነት ተቀጥረው የሚሠሩም አሉ።

ሳንታና በርካታ አፍሪካውያን ተመራማሪዎችን ለማፍራት በአፍሪካ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመተባበርም ትሠራለች።

ለዚህም ‘አፍሪካኮኔክት’ የሚል የአፍሪካ ተመራማሪዎች በአፍሪካ ጥናት እንዲያካሂዱ የሚያበረታታ አዲስ ፕሮግራም ጀምራለች።

የፕሮግራሙ ትኩረት በአፍሪካ ላይ ነው። ይህ ፕሮግራም የሳንታና ተማሪዎች በአፍሪካ ጥናት እና ምርምር ለማድረግ ድጋፍ የሚያገኙባቸውን ዕድሎች ለመፍጠር ያስችላል።

ፕሮግራሙ በጣልያን የትምህርት ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም በሌሎች ተቋማት ይደገፋል።