ከጥልቁ ውቅያኖስ ማዕድን ለማውጣት የሚካሄደው የኃያላን አገራት አዲሱ ፉክክር

ማዕድን ለማውጣት አሰሳ እያደረጉ ያሉ መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, The Metals Company

ቀጣናዊ የፖለቲካ ሽኩቻ ውሃ እና የብስን ተሻግሮ ዘንድሮ ወደ ጥልቁ ውቅያኖስ ዘልቋል።

ብዙ ሺህ ሜትሮችን ወደ ውስጥ ሰርጎ በባሕር ወለል ላይ ያሉ ማዕድናት ዓለም እያደረገች ላለችው የኃይል ሽግግር ወሳኝ ናቸው። ለአየር ንብረት ለውጥም አስፈላጊ መሆናቸው አያጠራጥርም።

በባሕር ወለል ላይ ያሉ ማዕድናት ወታደራዊ ቁሳቁስ እና የጦር መሣሪያ ለማምረትም ይፈለጋሉ።

ምንም እንኳ እስካሁን ከጥልቁ የውቅያኖስ ክፍል ማዕድናት ባይወጡም የግል ኩባንያዎች፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና ሕንድን የመሳሰሉ አገራት ፉክክር ላይ ናቸው።

በሰሜን ፓሲፊክ የሚገኘው ክላሪዮን ክሊፐርተን የተባለው ክፍል፤ በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ የሚገኘው ሚድ አትላንቲክ ሪጅ እንዲሁም ሕንድ ውቅያኖስ እና የፓሲፊክ ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል ላይ አሰሳ እየተካሄደባቸው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት አካል የሆነው ኢንተርናሽናል ሲቤድ የተባለው ባለሥልጣን [አይኤስኤ] ለአገራት እና ኩባንያዎች የአሰሳ ፈቃድ ይሰጣል።

ዩናይትድ ስቴትስ በድንበሯ ካሉ ጥልቅ ባሕራት ማዕድናት ለማውጣት ዝግጅት ላይ ትገኛለች። አሜሪካ ይህን የምታደርገው የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ስምምነትን ባለመፈረሟ ነው።

ይህ በመሆኑ በድንበሯ ከሚገኙ እንጂ ዓለም አቀፍ ከሚባሉ አሊያም የማንም አገር ንብረት ካልሆኑ የውሃ አካላት ማዕድን መቆፈር አትችልም።

አይኤስኤ እስካሁን 31 ፈቃዶች የሰጠ ሲሆን፣ 17 የሚሆኑት በሃዋይ እና በሜክሲኮ መካከል የሚገኘውን ክላሪዮን-ክሊፐርተንን እያሰሱት ይገኛሉ።

ይህ ሥፍራ ፖሊሜታሊክ ኖዱልስ የተባለው የድንች ቅርፅ ያለው የከበረ ድንጋይ የተከማቸበት ነው። ይህ ድንጋይ በውስጡ ማንጋኒዝ፣ ኮባልት፣ ኒኬል እና መዳብ ይዟል።

እነዚህና ሌሎች እንደ ሊቲየም እና ግራፋይት ያሉ ማዕድናት በኤሌክትሪክ የሚሠራ መኪና ለማምረት፣ ፀሐይ የሚቀበል መደብ ለመሥራት እና ከነፋስ ኃይል ለማመንጨት እንዲሁም ኃይል የሚሰበስቡ ባትሪዎችን ለማምረት ይጠቅማሉ።

ማዕድናት ለምን ተፈላጊ ሆኑ?

ከጥልቁ ውቅያኖስ ማዕድናትን ማውጣት አስፈላጊነቱ የጎላው ዓለም ወደ ታዳሽ ኃይል ሽግግር ማድረግ በመጀመሯ ነው።

በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖች ከነዳጆቹ ጋር ሲነፃፀሩ ስድስት እጥፍ ማዕድን ይፈልጋሉ። የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ደግሞ ከተፈጥሮ ጋዝ ጋር ሲነፃፀሩ 12 እጥፍ የማዕድን ፍጆታ ይሻሉ ይላል ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ።

የዓለም ባንክ ባወጣው መረጃ መሠረት ያለውን ፍላጎት በአውሮፓውያኑ 2050 ለማሟላት ጥልቁ ባሕር ውስጥ ያሉ ማዕድናትን የማውጣት ሂደቱ አምስት እጥፍ መጣደፍ አለበት።

ይህ ማለት የነፋስ፣ የፀሐይ፣ የእንፋሎት እና የሌሎችም ኃይል ክምችትን ለማሟላት 3 ቢሊዮን ቶን ማዕድን ያስፈልጋል ማለት ነው።

ከጥልቅ ውቅያኖስ ማዕድን ማውጣትን የሚደግፉ ባለሙያዎች በተለመደው መንገድ ማዕድን ማውጣት በቂ አይደለም፤ ይህ የሆነው ከየብስ የሚገኙ ማዕድናት ጥራት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት ከመሬት አስፈላጊ ማዕድናትን ቆፍሮ በማውጣት የተካኑት ጥቂት አገራት ብቻ ናቸው። አውስትራሊያ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሊቲየም አምራች ስትሆን፣ ቺሊ ደግሞ ቁጥር አንድ መዳብ አቅራቢ ናት።

ቻይና በዋናነት ግራፋይት እና ሌሎች ስልክ እና ኮምፒውተር ለማምረት የሚውሉ ማዕድናትን ቆፍራ በማውጣት ትታወቃለች።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኢንዶኔዢያ እና ደቡብ አፍሪካ ኮባልት፣ ኒኬል፣ ፕላቲኒየም እና ኢሪዲየምን በማምረት ይታወቃሉ።

ፖሊሜታሊክ ኖዱልስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና እና ማዕድን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቻይና ማዕድናትን ከራሷ ድንበር ባሻገር ካሉ የውሃ አካላት ለማውጣት ቁርጠኛ መሆኗ በቀጣናው ውጥረት ፈጥሯል።

አይኤስኤ ከሰጣቸው ፈቃዶች መካከል አምስቱ የቻይና ናቸው። ይህም ብዙ የውቅያኖስ ቁፋሮ ፈቃድ ያላት አገር ያደርጋታል። ሕንድ ሁለት ሲኖራት፣ ተጨማሪ ሁለት እንዲሰጣት ጠይቃለች። ሩሲያ አራት ፈቃዶች አሏት። አምስተኛውን ደግሞ ከሌሎች አገራት ጋር ትጋራለች።

“ቀጣናዊ ፖለቲካዊ ፉክክር አየተጧጧፈ ነው። አገራት አስፈላጊ የሚባሉ ማዕድናትን ከባሕር ወለል ቆፍረው አውጥተው ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሯሯጡ ነው” ይላሉ ሆራይዘን አድቫይዘሪ የተሰኘው ተቋም መሥራች ናታን ፒካሪሲች።

ነገር ግን ዋናው ስጋት የሆነው ነገር ቻይና እነዚህ ማዕድናት ወጥተው ለመገበያ ከመቅረባቸው በፊት ያለውን ሂደት መቆጣጠሯ ነው።

ቻይና ለዘመናት ማዕድናትን ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማሰናዳት ተክናለች። ግራፋይት እና ዲስፕሮሲየም አጣርታ ለገበያ የምታቀርበው ቻይና ብቻ ናት። 70 በመቶ የኮባልት እና 60 በመቶ የሊቲየም እና ማንጋኒዝ ማጣራት ሥራ የተያዘው በቻይና ነው።

ቤይጂንግ አንዳንድ የማጣሪያ ቴክኖሎጂዎች እና የተወሰኑ ብዙ የማይገኙ የብረት ዓይነቶችን ወደ ውጭ እንዳይወጡ አግዳለች።

ቻይና ይህን ያደረግኩት ራሴን ለመጠበቅ እና ብሔራዊ ደኅንነቴን እንዲሁም ፍላጎቴን ላለማስነካት ነው ትላለች።

ካለፈው ታኅሣሥ ጀምሮ ደግሞ የኤሌክትሪክ መኪና፣ የነፋስ ኃይል ማመንጫ እና ኤሌክትሮኒክ ለማምረት የሚውሉ ውድ ማግኔቶችን የሚያመርት ቴክኖሎጂ ከአገር እንዳይወጣ አግዳለች።

“እየተጋፈጥን ያለው የገበያ ኃይልን ተጠቅማ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት እየሞከረች ካለች ትልቅ አቅራቢ ጋር ነው” የሚሉት የአሜሪካ ኢነርጂ ሚኒስትር ጄኔፈር ግራንሆልም ናቸው።

ከሁለት ወራት በፊት የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ሠራዊት ኮሚቴ የአገሪቱ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን በባሕር ወለል ላይ ያሉ ማዕድናትን እንዲያስስ መመሪያ ሰጥቷል።

“በቅርብ ዓመታት ቻይና ከጥልቁ የውቅያኖስ ክፍል ፖሊሜታሊክ ኖዱልስ ለማውጣት እየተጣደፈች ነው። ይህን ለብሔራዊ ደኅንነት ለማዋልም አስባለች” ብሏል ኮሚቴው።

“ቻይና የዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለትን ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥረት ለመግታት አሜሪካ የራሷን መንገድ ማመቻቸት አለባት” ይላል ኮሚቴው።

አሜሪካ ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳ፣ ከፊንላንድ፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከስዊድን፣ ከጃፓን፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከአውሮፓ ኮሚሽን ጋር በ2022 የማዕድን ደኅንነት ስምምነት ገብታለች። ሕንድ እና ጣሊያን በቅርቡ ቡድኑን ተቀላቅለዋል።

ማዕድን ቆፋሪ ማሽን ውቅያኖስ ላይ

የፎቶው ባለመብት, The Metals Company

ቁፋሮው ለምን ተጓተተ?

ከጥልቅ ውቅያኖስ ማዕድን ማውጣት እስካሁን አልተጀመረም። ይህ የሆነው አይኤስኤ መመሪያ አውጥቶ ባለመጨረሱ ነው።

ሳይንቲስቶች እና የውቅያኖስ ደኅንነት ተቆርቋሪዎች የባሕር ጠለልን መቆፈር ከባቢያዊ ጉዳት አለው እያሉ እያስጠነቀቁ ነው።

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ሊሳ ሌቪን “ጥልቅ ባሕርን መቆፈር ምን ዓይነት አደጋ እንደሚያመጣ የምናውቀው ነገር የለም። እንዴትስ ልንመልሰው እንቸላለን የሚለውን አናውቅም። ውሃ ላይ ያለው ጉዳትስ፣ የዓሳ ምትርስ ምን ይሆናል የሚለውንም አናውቅም” ይላሉ።

ብራዚል፣ ካናዳ፣ ኮስታሪካ፣ ፊንላንድ፣ ስዊትዘርላንድ እና ቫኑዋቱን ጨምሮ 20 አገራት ተጨማሪ ጥናት እስኪደረግ ድረስ የጥልቅ ውቅያኖስ ቁፋሮ እንዳይጀመር ጠይቀዋል።

ይህም ቢሆን የኖርዌይ ፓርላማ ባለፈው ጥር በአርክቲክ ቀጣና አሰሳ እንዲጀመር የሚፈቅድ ረቂቅ አጽድቋል።

በርካታ አገራት የውቅያኖስ ጠለልን ቁፋሮ እንደ ትልቅ ዕድል ያዩታል።