የደቡብ ትግራይ አስተዳዳሪ የነበሩት ሃፍቱ ኪሮስ ከሥልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ወዴት ሄዱ?

አቶ ሃፍቱ ኪሮስ

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ትግራይ ዞን የቀድሞ አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞው የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳደርን በመቀየር ሁለት አዳዲስ አመራሮችን መሾሙን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት ተፈጥሯል።

ባለፈው ወር በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ ተግባራዊ የተደረገው ለውጥ "ሰላማዊ" ነው ቢባልም "በኃይል የታገዘ" በመሆኑ ሕዝባዊ ተቃውሞተቀስቅሶ ነበር።

በዚህም ምክንያት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ሞት እና ውድመት የደረሰ ሲሆን ጉዳዩ በድርድር ተፈትቶ የቀድሞ አስተዳዳሪ ወደ ሥልጠናቸው ተመልሰው ነበር።

ይህ ከተፈጠረ ከአንድ ወር በኋላ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ዝናቡ ገ/መድኅን የዞኑ አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸው ለጊዜው ጋብ ብሎ የነበረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ አገርሽቷል።

የቀድሞው አስተዳዳሪ ከሥልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ የት ገቡ ሲል ቢቢሲ ጠይቋቸዋል።

እየሆነ ያለው ምንድን ነው?

ከነሐሴ 18/2017 ዓ.ም. ጀምሮ አቶ ዝናቡ ገ/መድኅን የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ መሠራጨቱን ተከትሎ የአስተዳደሩን ቢሮ ሰብረው በመግባት ሥራ መጀመራቸው ይነገራል።

አቶ ዝናቡ እንደ ጨርጨር እና ሌሎች አካባቢዎች የተካሄዱ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ሲናገሩ ታይተዋል።

በመድረኮቹም ላይ ተሰብሳቢዎች "አሁንም እኛ አልመረጥንህም። በአፈ ሙዝ አንገዛም" ማለታቸውን በስብሰባው ላይ የተሳተፉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንን ያሉት በጨርጨር ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ መድረክ ላይ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

በዚህ ሕዝባዊ መድረክ ላይ አቶ ዝናቡ "ህወሓት ቢቀየም ኖሮ አንድም የሚቀር ሰው አይኖርም ነበር" ሲሉ መናገራቸው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተዘዋወረ ይገኛል።

የቀድሞው የዞኑ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ከሁለት ወራት በፊት እንዳደረጉት አሁንም "ሕዝባዊ ተቃውሞ" እያዘጋጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።

"በሥራ ላይ ነበርን፣ ካቢኔው ሥራ ላይ ነበር፣ ሁሉም ወረዳ ሥራ ላይ ነበር፣ የዞኑ ፖሊስ አስተዳደር እና የሚሊሺያ አስተዳደሮች ከአንድ ቀን በፊት ተጠርተው እንደነበር እናውቃለን" ብለዋል።

በአካባቢው በነበሩበት ወቅት ቢሮውን በኃይል ሰብረው እንደገቡም ተናግረዋል።

"አሁንም አካባቢው ላይ ነን። ሥራ ላይ እያለን ነው ሰብረው የገቡት።"

ቢቢሲ አቶ ሐፍቱ በአሁኑ ወቅት የት እነደሚገኙ የጠየቀ ሲሆን "በደቡብ ትግራይ ዞን ሕዝቡን እየመራን እና እያደራጀን ነው። በደቡብ ትግራይ ዞን ብዙ ሜዳዎች እና ሸለቆዎች አሉ። እዚያ ነው ያለነው" በማለት ከከተማ ወጣ ብለው ሕዝብን እያደራጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አንዳንድ የአካባቢው የሚሊሺያዎች እና የፖሊስ አባላት ከሕዝቡ ጎን መቆማቸው የተነገሩ ሲሆን፣ ሕዝባዊ ተቃውሞው ወደ ትጥቅ ግጭት ሊያመራ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

አቶ ሃፍቱ ሁኔታው ካልታረመ "ከሰላማዊ መንገድ አስወጥተውን ወደማንፈልገው የትግል መንገድ እየገፉን ነው" በማለት የትጥቅ ትግል እና ተቃውሞ ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።

የትጥቅ ትግል ለማድረግ ዕቅዳቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ "በቅርቡ አቋማችንን እናሳውቃለን" ብለዋል።

ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር የተነጋገሩት ምን ነበር?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ጋር ጥሩ መግባባት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሃፍቱ ኪሮስ "ፕሬዝዳንት ታደሰ ብቻቸውን ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እናውቃለን" ብለዋል።

በወቅቱ በመቀለ እና በማይጨው ከተማ በነበሩ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ሕዝቡ በመረጠው እንዲተዳደር፣ በኃይል አስተዳዳሪ መቀየር እንዲቆም ተሳታፊዎች ጠይቀው ነበር።

አቶ ሃፍቱ ይህንን የዞኑን አስተዳዳሪ የማንሳት ውሳኔ ያሳለፈው እርሳቸው ምክትል የሆኑበት "የኮማንድ ፖስት ኮሚቴ" ነው ሲሉ ይወነጅላሉ።

ዘጠኝ አባላት ያሉት የኮማንድ ፖስት ኮሚቴ ሊቀ መንበር በዶ/ር ደብረፂዮን የሚመራ ሲሆን፣ ከፍተኛ የህወሓት አመራር እና ወታደራዊ ባለሥልጣናትን ያካተተ ነው።

ስለኮሚቴው አመሠራረት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

ስለ መጨረሻው ስምምነት ይዘት የተጠየቁት አቶ ሃፍቱ "የጋራ መፍትሄ እንፍጠር፤ መላው ሕዝብ የሚሳተፍበት መድረክ ሊካሄድ ይገባል" የሚል መግባባት ላይ ተደርሶ እንደበር ተናግረዋል።

"ከእርሳቸው ጋር እንደተስማማነው ቢሆን ኖሮ በደቡብ ትግራይ ብቻ ሳይሆን በመላው ትግራይ ጥሩ ውጤት ይመጣ ነበር፤ ብዙ ምክክር አድርገናል" ብለዋል።

በዞኑ ስለተሾሙት አዲስ አመራሮች ከጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ ከሁለት ወራት በፊት በሰጡት መግለጫ የዞኑን ኃላፊዎች መሾም እና መሻር የፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ነው ብለዋል።

ላለፉት አራት ወራት በላይ በሥልጣን ላይ ያሉት ሌ/ጄ ታደሰ "ቀጣይ አደጋ ለማስወገድ እና የትግራይን ችግር ለመፍታት የአመራር ለውጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።

"ቀጣይ አደጋ" ግን ምን እንደሆነ በይፋ የተገለፀ ነገር የለም።

ከወራት በፊት ከሥልጣናቸው የተነሱት እና ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ የመሠረቱት አቶ ጌታቸው ረዳ የዚህ አካባቢ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በአካባቢው ከፍተኛ ድጋፍ አንዳላቸው ይታመናል።

ተመሳሳይ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ከዚህ ቀደም በተለይም በአዲግራት፣ በውቅሮ፣ በተምቤን፣ በመቀለ ከተማ እና እንደርታ ወረዳ ላይ ታይተዋል።

በደቡብ ትግራይ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ግን ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው።

ከዚህ በፊት "ኮር እና ከኮር በላይ" በሚል የተደረገውን ወታደራዊ ውሳኔን የተቃወሙ የትግራይ ኃይሎች ክልሉን ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስነው አካባቢ ራሳቸውን በማደራጀት የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የሚገኙት የትግራይ ታጣቂዎች በዞኑ የተካሄደውን እንዲሁም በአጠቃላይ በትግራይ ያለውን ወታደራዊ ውሳኔ እና እርምጃ ተቃውመዋል።

እነዚህ ታጣቂዎች ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከሁለት ጊዜ በላይ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው በሰው ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።

የትግራይ የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ጥቃቱን ተከትሎ በአቶ ጌታቸው የተቋቋመው ስምረት ፓርቲ ከጀርባው አለ ሲል ወንጅሏል።

አቶ ጌታቸው ግን ፓርቲያቸው እጁ አንደሌለበት በመግለጽ ክሱን አስተባብለዋል።

ወዴት እያመራ ነው?

በደቡብ ትግራይ ነባር አመራሮችን አውርዶ በአዲስ የመተካት አንቅስቃሴ ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት በነዋሪዎች ዘንድ ተፈጥሯል።

"ሽማግሌዎቹ አሁንም ተዉ እያሉ ነው" ያሉት ሃፍቱ ኪሮስ፤ አሁንም ሽማግሌዎች ወደ ክልሉ እየተላኩ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።

ይህ አዲሱ አስተዳዳሪ የአካባቢው ተወላጅ ነው። አሁን ተቃውሞ ውስጥ ያስገባችሁ ምንድን ነው? ተብለው የተጠየቁት አቶ ሃፍቱ "የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በአገሬ ሰው መመራት አለብኝ ማለት ብቻ አይደለም፤ ራሴ የመረጥኩት፣ ራሴ የወከልኩት፣ የእኔ ድምጽ ያለው መሪ ነው የሚያስፈልገን ማለት ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

"የደቡብ ትግራይ ሕዝብ እስካሁን ትግራዋይ ነኝ ብሎ እየታገለ ነው። ከተለያዩ መድረኮች ተገልሏል" ሲሉም ተናግረዋል።

ኮር እና ከኮር በላይ በሚል በተካሄደው ጉባዔ ላይ የህወሓት አባላት የሆኑ የአካባቢው ተወላጆች ተገልለዋል ያሉት አቶ ሐፍቱ፣ የደቡብ ትግራይ ሕዝብ ያልተሳተፈባቸው ጉባዔዎች ናቸው በማለት ቅሬታው ስር የሰደደ መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ዝናቡ ገ/መድኅን በጨርጨር ከተማ በተካሄደ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ "መንግሥት አንደ መንግሥት ቢቀየም ኖሮ፣ ህወሓት እንደ ህወሓት ቢቀየም ኖሮ የሚቀር ሰው አይኖርም ነበር። ብዙ ስህተቶች ተፈጽመዋል። እንደ ጨርጨር ተወላጆች፣ እንደ ታጋይ፣ ሁሉንም ሰው በፈጸመው ስህተት አሳደን ተጠያቂ ማድረግ አንፈልግም" ማለታቸው ተዘግቧል።

ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተቆርጦ የሚዘዋወረው የአዲሱ ተሿሚ ንግግር እንዲሁም ተፈጽሟል ያሉት በደል ምን አንደሆነ እና በምን አውድ እንደተናገሩት ቢቢሲ ማጣራት አልቻለም።