የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአክሱም ሙስሊም ተማሪዎች "ሂጃብ ለብሰው እንዲማሩ" ወሰነ

የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩት የአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች "ሂጃብ ለብሰው እንዲማሩ" ውሳኔ መሰጠቱን ፍርድ ቤቱ ገለጸ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች "በእስላማዊ አለባበሳቸው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ" የተላለፈው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ "ተፈፃሚነት እንዲረጋገጥ" ጠይቋል።
ከህዳር ወር ጀምሮ ትምህርታቸውን በማቋረጣቸው ሀገር እና ክልል አቀፍ ፈተናዎች ያመለጧቸው የአክሱም ከተማ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች በበኩላቸው "ያለፋቸው ትምህርት እንዲካካስላቸው" ጠይቀዋል።
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 15/2016 በዋለው ችሎት እንደሆነ የፍርድ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ እሸቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በክልሉ ትምህርት ቢሮ ላይ ክሱን የመሰረተው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንደሆነም ገልጸዋል።
የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው በአክሱም ከተማ የሚገኙ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው እንዳይገቡ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ክልከላ በመጣላቸው ነበር።
ይህንን እገዳ ካደረጉት የአክሱም ትምህርት ቤቶች መካከል አክሱም፣ ቀዳማዊ ሚኒሊክ እና አሉምናይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል።
ክንደያ አንደኛ ደረጃ እና አብርሃ አፅብሃ ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ ሂጃብ የሚለብሱ ሙስሊም ሴት ተማሪዎችን አግደዋል።
ክልከላውን ለማስፈጸም የፖሊስ አባላት በትምህርት ቤቶች ደጃፎች ላይ ተሰማርተው እንደነበረ እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳረጉ ተማሪዎች እንደነበሩ ተማሪዎች እና ወላጆች በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ቢቢሲ አሁን ያነጋገራቸው ተማሪዎች፤ ከስድስተኛ እስከ 12 ክፍል ያሉ የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከህዳር አንስቶ ትምህርታቸውን አቋርጠው መቆየታቸው አስረድተዋል።
በዚህ ምክንያት ተማሪዎቹ በዚህ ዓመት መውሰድ የነበረባቸው የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እንዲሁም የስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናዎቹ እንዳመለጧቸው ገልጸዋል።
አንዲት የአክሱም ሁለተኛ ትምህርት ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪ፤ እሷን ጨምሮ ከዘጠኝ እስከ 12ተኛ ክፍል ያሉ "250 ገደማ" ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ዘንድሮ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ የነበረችው ተማሪዋ፤ "አንሰጥም አትፈተኑም ብለውን ፈተናው አምልጦናል። ሂጃብ አውጥታችሁ ካልሆነ አትገቡም አሉ" ስትል ሀገር አቀፍ ፈተና እንዳለፋት አስረድታለች።
ሌላ የክንደያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ በበኩሏ "ትምህርት አቋርጠሻል" በሚል የመፈተኛ ካርድ (admission card) መከልከሏን ተናግራለች።
አንዳንድ የስድተኛ ክፍል ተማሪዎች "ሂጃብ አውልቀው" ትምህርት ከቀጠሉ በኋላ ክልል አቀፍ ፈተና መውሰዳቸውንም ጠቅሳለች።
ይህንን እርምጃ የተቃወመው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በመጀመሪያ ክስ መስርቶ የነበረው በአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት እንደ ነበር የጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።
"የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት 'ይሄ ጉዳይ የእኛ ስልጣን አይደለም፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን ነው' ብሎ መዝገቡን ዘጋው። ከዚያ በትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደ አዲስ ክስ ገብቶ [ታይቷል]" ሲሉ ሂደቱን አስረድተዋል።
የሁለቱን ወገኖች ክርክር ሲመለከት የነበረው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት "ሂጃብን የሚከለክል የህገ መንግሥት [ድንጋጌ] የለም። ስለዚህ ሂጃባቸውን አድርገው እንዲማሩ" በሚል በውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ በውሳኔው ላይ "ለሰበር ይግባኝ የማቅረብ መብት" እንዳለውም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, sm
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ውሳኔውን በተመለከተ ትናንት ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስቷል። ምክር ቤቱ፤ "የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች እስላማዊ አለባበሳቸውን ለብሰው መማር ህገ-መንግስታዊ መብታቸው መሆኑ ተወስኗል" ብሏል።
ተማሪዎቹ "እስላማዊ አለባበሳቸውን ጠብቀው (ለብሰው) መማራቸው ህገ-መንግሥታዊ መብታቸው" እንደሆነ በፍርድ ቤቱ መወሰኑንም ጠቅሷል።
"የአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በእስላማዊ አለባበሳቸው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላልፏል" ሲልም የተሰጠውን ትዕዛዝ አስታውቋል።
ምክር ቤቱ፤ "ከትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጋር በመሆን ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል" እንደነበር ጠቅሶ፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "በበጎ እንደሚመለከተው" ገልጿል። የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ "ተፈፃሚነቱ እንዲረጋገጥም" ጠይቋል።
የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች "ሂጃባችሁን ካላወለቃችሁ አትማሩም" ተብለው ከትምህርት መታገዳቸውን ያስታወሰው ምክር ቤቱ፤ በዚህ የተነሳም የ12ተኛ እና 8ተኛ ክፍል ፈተናዎች ሳይፈተኑ መቅረታቸውን ገልጿል።
"ተማሪዎቹ ለአንድ አመት ያክል ሲንገላቱ እና አብዝተው የጓጉለትን ትምህርት ሳይማሩ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ፈተናዎች ላይም ሳይቀመጡ ቀርተዋል" ብሏል። በዚህ ምክንያት "የደረሰው ጉዳትም ከፍተኛ መሆኑን" እንደሚያምንም በመግለጫው አንስቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎችም በእገዳው ምክንያት "አንድ ዓመት ወደኋላ መቅረታቸውን" ገልጸዋል።
ሙሩአይን መሀመድ የተባሉ አንዲት እናት የ8ተኛ ክፍል ተማሪ የነበረች ልጃቸው "አንድ ዓመት ወደኋላ መቅረት በጣም እንደሚያሳስባቸው" ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዊልዳን አደም የተባለች የአሉምናይ ሁለተኛ ደረጃ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪም፤ "ከጓደኞቻችን በታች ቀርተናል። ወደ ኋላ የቀረነው በእነሱ ምክንያት ነው። በጣም ተጽዕኖ ፈጥሮብናል" ስትል ተመሳሳይ ሀሳብ አንስታለች።
ዘጠነኛ ክፍልን "መድገም ብዙ ተጽዕኖ" እንዳለው የምትገልጸው ዊልዳን፤ "ከጓደኞቻችን እኩል መሆን ነው የምንፈልገው" ብላለች።
ሌላ የአክሱም ሁለተኛ ትምህርት ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪ በበኩሏ "ዓመት ሙሉ [ትምህርት] አልፎናል። ከጓደኞቻችን ኋላ ቀርተናል። ያለፈንን ትምህርት ቢክሱን ደስ ይለናል" በማለት ሀሳቡን ተጋርታለች።
"እኛ 12ተኛ ክፍል ነን። የእኛ ጓደኞች ተፈትነው አልፈዋል። ዘጠነኛ ክፍል የነበሩም የእነሱ ጓደኞች አሁን 10 ገብተዋል። ትምህርቱን አፋጥነው ከጓደኞቻችን እኩል ቢያደርጉን ደስ ይለናል" ስትል ፍላጎቷን ገልጻለች።
ቢቢሲ ውሳኔውን በተመለከተ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የአክሱም ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጸጋ ገብረመስቀል በበኩላቸው "ምን እንደተወሰነ አላወቅንም፤ አልተነገረንም" በማለት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በተመለከተ "መረጃ እንደሌላቸው" ተናግረዋል።















