በደቡብ ትግራይ መኾኒ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ስላደረሰው የተኩስ ልውውጥ የምናውቀው

የፎቶው ባለመብት, SM
በደቡብ ትግራይ በራያ አዘቦ ወረዳ መኾኒ ከተማ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ከነዋሪዎች ጋር የፈጠሩትን ግጭት ተከትሎ በከፈቱት ተኩስ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ቢቢሲ ትግርኛ ከነዋሪዎች፣ ከቤተሰቦች እና ከሕክምና ባለሙያዎች ሰምቷል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በትግራይ "አርሚ 43" ዕዝ አባላት በአካባቢው በተሰማሩበት ጊዜ በተፈጠረ አለመግባባት ግጭት ተፈጥሮ በወሰዱት እርምጃ መሆኑን የዓይን እማኞች ይናገራሉ።
የዕዙ አባላት የራያ አዘቦ ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ሐለፎም መሃሪን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሞከሩበት ወቅት በከተማዋ ከሚገኘው 'ሀመድ መኾኒ' ከሚባል የወጣቶች አደረጃጀት አባላት ጋር ተጋጭተው እንደበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ሰኞ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ ግጭቱ የተፈጠረበት ስፍራ እንቅስቃሴ የሚበዛበት እና የንግድ አካባቢ መሆኑን በስፍራው የነበረው ሀብቶም የተባለው የከተማዋ ነዋሪ ይናገራል።
ኮሎኔል ሐለፎም መሃሪን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ የዕዙ አባላት ወደ አካባቢው መምጣታቸውን የሚናገረው ሀብቶም፣ "በሕግ ከተፈለገ የፍርድ ቤት ወረቀት አምጥታችሁ ውሰዱ። እርሱ የሚታሰር ከሆነ ራሳችን እናስረዋለን" በማለት በአካባቢው በሚገኙ ሚሊሻዎች እና ታጣቂዎች መካከል ግጭት መፈጠሩን ይናገራል።
ታጣቂዎቹ የአርሚ 43 ዕዝ አባላት መሆናቸውን የገለፀው ሀብቶም፤ ሲቪል ለብሰው መምጣታቸውንም ጨምሮ ያስረዳል።
ቢቢሲ የሚሊሻ አዛዥ የሆኑትን ኮሎኔል ሐለፎም የተፈለጉበትን ምክንያት ለማጣራት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ሆኖም ኮሎኔሉ በተኩስ ልውውጥ መካከል እንዳመለጡ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች ነዋሪዎች ተኩሱ ለአንድ ሰዓት ያህል መቆየቱን ገልጸው፤ ተደናግጠው "ምን አንደተፈጠረ ለማወቅ የወጡ" ነዋሪዎች በተኩሱ ተጎጂ ሆነዋል ብለዋል።
በዚህም አምስት ሰዎች ተጎድተው ሆስፒታል መወሰዳቸውን የተናገሩት ነዋሪዎች ሁለቱ ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸዋል ብለዋል።
የመኾኒ ሆስፒታል ዳይሬክተተር የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል በርሄ ለቢቢሲ አምስት ሰዎች በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
"አምስት ሰዎች ናቸው የመጡት። ሁለቱ ከባድ፣ ሦስቱ ግን ቀላል ጉዳት አጋጥሟቸዋል።"
"አንዱ በእግሩ ላይ፣ ሁለቱ እጃቸው ላይ ጉዳት አጋጥሟቸዋል። ከባድ ጉዳይ ያጋጠማቸውን ሁለቱን ግን ወደ መቀለ ለተሻለ ሕክምና ልከናል" ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ዳንኤል ለተሻለ ሕክምና ስለተላኩ ሰዎች ሲናገሩ "አንዱ በአንገቱ የገባች ጥይት በጀርባው ወጥታለች። እግሩም ዝሏል። ሌላኛው ደረቱ ላይ የተመታ ሲሆን ብዙ ደም ፈስሶታል። ደም ሰጥተነው ሁለቱንም ወደ መቀሌ ልከናቸዋል" ብለዋል።
ትዕግሥት ኃይሌ የተባለች ነዋሪ በበኩሏ ባለቤቷ በጥይት ተመትቶ በሪምና ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ተናግራለች።
ባለቤቷ አቶ ዝናቡ የአዲግራት ዩኒቨርስቲ መምህር መሆኑን እና "ጥይት በጉሮሮው ገብታ በጀርባው ወጣች" ስትል ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግራለች።
አቶ ዝናቡ የተመታው በአጋጣሚ በአካባቢው እያለፈ በነበረበት ወቅት መሆኑንም አክላ ተናግራለች።
ዶ/ር ዳንኤል የተጎጂዎቹን ሁኔታም ሲገልፁ ሁሉም ወንዶች እንዲሁም ዕድሜያቸው በ20 እና 30ዎቹ መካከል አንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከተጎጂዎች መካከል አንድ ግለሳብ ብቻ በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ሰኞ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም. በደቡብ ትግራይ መኾኒ ከተማ የተኩስ ልውውጡ የተፈጠረው የአካባቢው ሕዝብ በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት በመሆኑ ግርግር እና ውዥንብር ተፈጥሮ እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ያስረዳሉ።
ክስተቱን ተከትሎ ሕዝቡ የታጠቁ ኃይሎች ከአካባቢው እንዲወጡ ጠይቋል።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የአርሚ 43 ዕዝ አባላት ተኩስ ከፍተው ሁለት የመብራት ኃይል ሠራተኞችን በማቁሰል ይወነጀላሉ።
ቢቢሲ የዕዙን አዛዥ ኮሎኔል ትንሳኤ ብርሃኔን ያነጋገረ ሲሆን፣ የቀረበባቸውን ክስ "ስም የማጥፋት ውንጀላ ነው" በማለት አጣጥለውታል።
"የእኛ ሠራዊት ለሕዝብ የሚታገል እንጂ ሕዝብ የሚያጠቃ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።
ቢቢሲ ለኮሎኔሉ ተጨማሪ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ሐምሌ 21/ 2017 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በክልሉ ደቡባዊ ዞን የአስተዳዳሪዎች ሹም ሽር ማድረጋቸውን ተከትሎ ነባሩ አመራር ለምን ከሥልጣን ተነሳ እንዲሁም የወረዱበትን ሂደት በመቃወም በመኾኒ እና አካባቢዋ የተቃውሞ ሠልፎች ተካሂደዋል።
በመኾኒ ከተማ ወደ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች በትጥቅ የታገዘ ነው ያሉት የነባር አመራሮችን መቀየር በማውገዝ "በህወሓት አንመራም"፣ "በጠመንጃ አፈሙዝ አንገዛም"፣ "ጭቆና ይቁም" የሚሉ መፈክሮችን አሰምተው ነበር።















