በደቡባዊ ትግራይ የተካሄደው ተቃውሞ እና ውጥረት

ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, HB

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በክልሉ ደቡባዊ ዞን የአስተዳዳሪዎች ሹም ሽር ማድረጋቸውን ተከትሎ ነባሩ አመራር ለምን ከሥልጣን ተነሳ እንዲሁም የወረዱበትን ሂደት በመቃወም እየተደረጉ ያሉ የአደባባይ ሰልፎች ቀጥለዋል።

ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ እሁድ በመኾኒ ከተማ እንዲሁም በትናንትናው ዕለት ሰኞ፣ ሐምሌ 21/ 2017 ዓ.ም. በአምባላጌ የአደባባይ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።

እነዚህ የአደባባይ ተቃውሞዎች ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ ዞኖች ተስፋፍቶ እሁድ ዕለት በወጅራት ኢስራ ዓዲ ውረዳ እንዲሁም ዓዲጉደም የተቀሰቀሱ ሲሆን፣ በዚህም ሞት መከሰቱን እንዲሁም እስሮችም መፈጸማቸው ተዘግቧል።

በመኾኒ ከተማ ወደ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች በትጥቅ የታገዘ ነው ያሉት ነባር አመራሮች መቀየርን በማውገዝ "በህወሓት አንመራም"፣ "በጠመንጃ አፈሙዝ አንገዛም"፣ "ጭቆና ይቁም" የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ነባሩ የደቡባዊ ዞን አስተዳደር ከሥልጣን ወርዶ በአዳዲስ ተሿሚዎች እንደሚተካ ውሳኔያቸውን ሐምሌ 15/ 2017 ዓ.ም. ባስታወቁበት ወቅት "በቀጣይ ሊከተሉ የሚችሉ አደጋዎችን ለማስቀረት" ያለመ እንደሆነ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚደረገው ለውጥ በዞን ደረጃ እንደሆነ በወቅቱ ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ አስተዳደሩ ፈርሶ እንደ አዲስ መዋቀሩን እና ነባሩ አስተዳደር ከሥራ ውጪ መሆኑን አስታውቀው ነበር።

በዞኑ አመራር ስፍራ ላይ የነበሩ ግለሰቦች በክልሉ አስተዳደር ሌሎች የኃላፊነት ቦታዎች እንደሚመደቡም በወቅቱ ተገልጾ ነበር ።

ወጅራት ዒስራ ዓዲ ወረዳ ከነበረ የአደባባይ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ እስር እና ሞት ያጋጠመ ሲሆን፣ በዚህም አንድ አርሶ አደር መገደላቸው እና የሁለት ሚዲያ ጋዜጠኞች ታስረው እንደነበር ተገልጿል።

የትግራይ የግል መገናኛ ብዙኃን የሆኑት ቲቢኤስ ቴሌቪዥን እና ቲፒኤም ተቃውሞውን ለመዘገብ የሄዱ ጋዜጠኞቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር እና በኋላም መለቀቃቸውን ገልጸዋል።

ታጣቂዎች የካሜራ ባለሙያውን ቪዲዮ እንደይቀርጽ እንዳስፈራሩም ገልጸዋል።

ሚዲያዎቹ ተቃዋሚዎቹ ጣልቃ ሊገቡ በሞከሩበት ወቅት ፖሊስ ተኩስ ከፍቶ አንድ ሰው መገደሉን በጋራ መግለጫቸው አስረድተዋል።

የቲፒኤም ዋና አዘጋጅ አድሃኖም ሰርጸ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገሩት "ጋዜጠኞቻችን ከከባድ ጥረት እና የሞት ስጋት በኋላ በሰላም ተገኝተዋል። መቀለ ከመጡ በኋላ የታዘብነው ድንጋጤ እና ሽብር በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በሚገባ አሳይቷል" ብለዋል።

አድሃኖም ጋዜጠኞቹ በዓዲ ጉደም ባህሪ ጸባ ጣቢያ በተባለ ስፍራ የታቀደ ሕዝባዊ መድረክን ሪፖርት ለማድረግ ወደ ከተማዋ ማቅናታቸውን ተናግረዋል።

ዓዲ ጉደም ሲደርሱ "ህድሞ በሚባል አካባቢ በታጣቂ ኃይሎች መያዛቸውን" አድሃኖም ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጋዜጠኞቹ ከሦት ሰዓታት በኋላ ቢፈቱም ወደ መቀለ መመለስ እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት ጋዜጠኞች ጋር ቪዲዮ አትቅረጹ በሚል በተነሳ ግጭት የአንድ አርሶ አደር ሕይወት ማለፉን የዓይን እማኞች የተናገሩ ሲሆን፤ የአርሶ አደሩ ቀብር ሥነ ሥርዓትም በትናንትናው ዕለት ተፈጽሟል።

የደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ ምን ይላሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገው የነበሩት የደቡባዊ ዞን አስተዳደር እንዲሁም መዋቅሩ ወደ ኃላፊነቱ እንዲመለስ ከታደሰ ወረደ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሐፍቱ ኪሮስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ሐፍቱ ኪሮስ ተደረሰ ስላሉት ስምምነት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት በኩል የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም። የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን አስመልክቶ የዘገቡት የለም።

"እሁድ፣ ሐምሌ 20/2017 ዓ.ም. ጠዋት ከ2፡00 አስከ 8፡00 ውይይት ነበረን፤ ዋናው ጥያቄ የካቢኔው መቀጠል አለመቀጠል ሳይሆን፤ የሕዝብ ጥያቄ ይመለሳል ወይስ አይመለስም የሚለው ነበር።

"በዚህ ውይይት የደቡብ ትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያስችለው ሁኔታ አመቻችቷል። ዞኑ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲህ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ትልቅ ድል ነው" ሲሉ የቀድሞ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሐፍቱ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ ምሽት የአድማ በታኝ ፖሊስ እና ሠራዊት በማይጨው እና መኾኒ በተሰማራበት ወቅት አቶ ሐፍቱ ኪሮስ፣ ካቢኔው እና ከተቀረው አመራር ጋር ከተሞቹን ለቀው መሄዳቸው ተነግሯል።

በዞኑ የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ ከትግራይ ደቡባዊ ዞን ወረዳዎች የተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ወደ መቀለ በመሄድ ከትግራይ ጊዜያዊ ፐሬዚዳንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ጋር ንግግሮችን አድርገዋል።

ውይይታቸውን ተከትሎ ጄነራል ታደሰ ወረደ ወደ ደቡባዊ ትግራይ ዞን መቀመጫ ማይጨው አቅንተው ከአገር ሽማግሌዎች እና ከሕዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በተጨማሪም የዞኑ ካቢኔ ከጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ካደረገው ውይይት በኋላ በስፍራው ተሰማርተው የነበሩ አድማ በታኞች እየወጡ እንደሆነ አቶ ሐፍቱ ገልጸዋል።

"በመኾኒ የተሰማሩ አድማ በታኝ ፖሊሶች እሁድ ዕለት ወጥተዋል፤ ከማይጨው ደግሞ ሰኞ እየወጡ ነበር። የትግራይ ሠራዊት በስፍራው እንዳለ ነው። ሠራዊቱ በደቡባዊ ዞን የተሰማራበት ሁኔታ ከሕግ ውጪ ስለሆነ አልተቀበልነውም" ብለዋል።

የአድማ በታኞቹ ከእነዚህ ስፍራዎች ወጥተዋል መባሉን ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።

ከትግራይ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንትም ሆነ ከባለሥጣናቱ ቢቢሲ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

አቶ ሐፍቱ ተጠሪነታችሁ ለማን ነው? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር አብረን እንሠራለን የሚል ምላሽ ሰጥተናል።

"ሁላችንም ተጋሩ ነን። የትግራይን ሥርዓት ነው የምንከተለው። ህወሓትን ተከትልንም አልተከተልንም ተጠሪነታችን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ነን። ትግራይ የህወሓት ብቻ ልትሆን አይገባም" ብለዋል።

የዞኑ ውጥረት እንዴት ወደዚህ አመራ?

ከሦስት ወር በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ የደቡባዊ ዞን አስተዳደር ሹም ሸርን አስመልክቶ በሰጡት መገለጫ በክልሉ የተፈጠረው የአስተዳደር ለውጥ ሰላማዊ ቢሆንም "ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የፀጥታ ኃይል ተልኳል" ብለዋል።

ለዚህ ውሳኔያቸው መንስዔ "በቀጣይ ሊከተሉ የሚችሉ አደጋዎች ለማስቀረት" ያለመ እንደሆነ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

የህወሓት መከፈልን ተከትሎ በአቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው ኃይል ጋር የተሰለፉት የትግራይ የደቡባዊ ዞን አስተዳደር አካላት፣ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች እና ወረዳዎች የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅሮችን መፍረሳቸውን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

እንዲሁም በወቅቱ ጊዜያዊ አስተዳደር በነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ተሹመው የነበሩ የተወሰኑ አመራሮችን መተካትንም ተቃውመዋል። እየተተኩ የነበሩት አመራሮች ከአሁኑ አገራዊ ምርጫ በፊት በክልሉ እንዲሁም በመላው አገሪቷ በነበረው ምርጫ በወረዳ እንዲሁም በከተሞች ምክር ቤቶች የተመረጡ አመራሮች መሆናቸው በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍን የሚደግፉ የትግራይ ሠራዊት አዛዦች መሪነት ጽህፈት ቤቶችን በኃይል ተቆጣጥረዋል የሚልም ተቃውሞም መሰማቱ ይታወሳል።

የቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ይህንን የአሁኔ ውሳኔ የህወሓት አመራር እና ኤርትራ በጋራ እየሠሩ መሆኑን በመዘርዘር አስተዳደሩ በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ ዞኖች "ወታደራዊ ዘመቻ በማድረግ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ ሙከራ አድርጓል" ሲሉ ከስሰዋል።

ሆኖም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ የዞኑ አስተዳደሮችን መሾምና የመሻር ሥልጣን የፕሬዚዳንቱ ነው ብለዋል።