በደቡብ ትግራይ የፀጥታ ኃይሎች "የአስተዳደር ለውጥ" ለማድረግ መሰማራታቸውን ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Tigrai TV
በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን የአመራር ለውጥ እየተደረገ መሆኑን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በክልሉ የተፈጠረው የአስተዳደር ለውጥ ሰላማዊ ቢሆንም "ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የፀጥታ ኃይል ተልኳል" ብለዋል።
የዞኑ አመራር ለውጡ የሚያስተባብሩት አቶ አስመላሽ ረዳ መሆናቸውን የገለፁት ሌ/ጄነራል ታደሰ፣ የዞኑ ፀጥታ ኃላፊ አቶ ንጉሤ አበጀ እንዲሁም አቶ ካላዩ ግደይ እና ወ/ሮ ዓለም ኃላፊነት እንደተሰጣቸው በመግለጫው ላይ ጨምረው ተናግረዋል።
ነገር ግን ከእነዚህ ኃላፊዎች መካከል አንዳንዶቹ ጉዳዩን እንደማያውቁ እና ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ ጽፈዋል።
የደቡብ ዞን አመራሮች ይልቁንም ነባሩን አመራር እንደሚደግፉ እና ለውጡን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።
የአቶ ጌታቸው አስተዳደር ሥልጣን መስረከቡን ተከትሎ የክልሉ ደቡባዊ ዞን አመራሮች ተቃውሟቸውን ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንትናው ዕለት በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ የህወሓት አመራር እና ኤርትራ በጋራ እየሠሩ መሆኑን በመዘርዘር አስተዳደሩ በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ ዞኖች "ወታደራዊ ዘመቻ በማድረግ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ ሙከራ አድርጓል" ሲሉ ከስሰዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ የዝናብ ወቅት፣ ጥረቶች ሁሉ ወደ ሰላም መሆን እያለባቸው "በሕዝባችን ላይ ጦርነት መርጠዋል" ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ወንጅለዋል።
አቶ ጌታቸው ይህንን የኤርትራ እና የትግራይ ኃይሎች "ያልተቀደሰ ጥምረት" በማለት የጠሩት ሲሆን "ዳግም በሕዝባችን ላይ ጦርነትን ማወጅ" ነው ሲሉ ኮንነውታል።
የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ቀደም ሲል ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገሩት በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች እንደተደረገው ማህተምን በጉልበት የመንጠቅ እርምጃን አንቀበልም ብለው ነበር።
አሁን በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እየተወሰደ ያለው ይህ እርምጃ አካባቢውን ወደ ግጭት ውስጥ እንዳያስገባው ስጋት ፈጥሯል።
መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በነበሩት ወቅት ከፍተኛ የትግራይ ኃይል አዛዦች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በኃይል የአመራር ለውጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከዚያ በኋላም የፌደራል መንግሥቱ ሁለት ዓመት ያገለገሉትን አቶ ጌታቸው ረዳን በማንሳት፣ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾሟል።
ላለፉት ሦስት ወራት ትግራይን በማስተዳደር ላይ ያሉት አቶ ታደሰ ወረደ ዛሬ ጠዋት በሰጡት መግለጫ "መንግሥት ማድረግ ያለበትን እየሠራን ነው፤ ነገርግን ይህ እርምጃ አካባቢውን ለማወክ ያለመ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት" ብለዋል።
ቀደም ሲል የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል ወደ ደቡብ ትግራይ ለመግባት መወሰናቸውን ተናግረው ነበር።
"... በደቡብ ዞን ችግር ያለበት አስተዳደር አለ... አስተዳደሩ ከቡድኑ [ከእነ ጌታቸው] ጎን ሆኖ እስካሁን ያልተስተካከለ እና ለውጥ ያልተደረገበት አካባቢ ነው" ብለው ነበር።
ባለፈው ሚያዝያ ወር በደቡብ ትግራይ ዞን ማይጨው እና አላማጣ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የአስተዳደር ለውጡን በመቃወም በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል።
ተቃውሟቸውን ያሰሙት እነዚህ ሠልፈኞች በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ በመቃወም በጠመንጃ ሥልጣን ለመያዝ ያለው ፍላጎት ለተቃውሞው ምክንያት መሆኑን ተናግረው ነበር።
በህወሓት አመራር መካከል የተፈጠረውን መቃቃር ተከትሎ ክፍፍሉ ወደ ትግራይ ኃይሎች ከተሸጋገረ በኋላ፣ ከፍተኛ አዛዦች በደብረፂዮን ገብረሚካኤል ከሚመራው የህወሓት ክንፍ ጎን መሰለፋቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ከትግራይ ኃይሎች እራሳቸውን የነጠሉ አዛዦች እና ታጣቂዎች በእነዚህ አካባቢዎች እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲሆን፣ ከሳምንታት በፊት ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ተዘግቧል።















