'የነጻ መሬት ታጣቂዎች በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት ሰነዘሩ' - የትግራይ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ

ራሳቸውን 'የትግራይ ሰላም ኃይል' ብለው የሰየሙት እና ትግራይ እና አፋር በሚዋሰኑበት አካባቢ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ራሳቸውን 'የትግራይ ሰላም ኃይል' ብለው የሰየሙት እና ትግራይ እና አፋር በሚዋሰኑበት አካባቢ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች

የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ታጣቂዎች ምላዛት በተባለው አካባቢ በሰፈረው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይል ላይ ጥቃት አድርሰዋል ሲል ከሰሰ።

ቢሮው ሐሙስ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ በአካባቢው በሚገኘው የትግራይ ታጣቂዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት አንድ አባል መሞቱን አስታውቋል።

ረቡዕ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም. በተፈጠረው ግጭት የተገደለው የትግራይ ኃይሎች አባል አንዳይ ክንደያ የተባለ መሆኑንም ገልጿል።

ትግራይ ክልል ከአፋር ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ የሚነገርላቸው እና በተለምዶ "ሓራ መሬት" (ነጻ መሬት) ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች፣ ከትግራይ ኃይሎች ተነጥለው የወጡ ናቸው።

እነዚህ ታጣቂዎች በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ እና ድርጅቱን የሚደግፉ የትግራይ ኃይሎች አዛዦች ከሥልጣን ለማስወገድ ወደ አፋር ክልል ሄደው መደራጀታቸውን ይናገራሉ።

በቅርቡ ራሳቸውን 'የትግራይ ሰላም ኃይል' ብለው የሰየሙት እነዚህ ታጣቂዎች በደቡብ ምሥራቅ በኩል ከትግራይ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።

መግለጫው አክሎም 'በነጻ መሬት' ስም እያሳሳቱ ያሉት ታጣቂዎች፣ "በውጭ ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው እና በስምረት ፓርቲ እየተመሩ የትግራይ ተወላጆች እርስ በርስ እንዲጋጩ እያደረጉ ነው" በማለት ከስሷል።

ስምረት ፓርቲ በቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ በሆኑት በአቶ ጌታቸው ረዳ እና በሌሎች የቀድሞ ህወሓት አባላት የተመሠረተ አዲስ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይሄንን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ለሊቱን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በሰጡት መልስ፣ ቢሮው "የትግራይን ኅልውና አደጋ ላይ የሚጥል የወንጀል መረብ አካል ነው" በማለት በገንዘብ ማጥፋት ወንጀል ከስሷል።

አቶ ጌታቸው በክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በእሳቸው እና በአዲሱ ፓርቲያቸው ላይ የተሰነዘረውን ክስ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ 'ስምረት ወታደር እና ገንዘብ የለውም' በማለት በግጭቱ ውስጥ እጁ እንደሌለበት አስተባብለዋል።

የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በመግለጫው ላይ በአላማጣ ከተማ በዚህ ሳምንት በአንድ ቤተሰብ ላይ ለተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ የፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂ መሆናቸውንም አመልክቷል።

ቢሮው፣ በአካባቢው የተለያዩ የፀጥታ ኃይሎች ቢገኙም አላማጣ ከተማ በኮማንድ ፖስት ስር መሆኗን እና ''የፌደራል መከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አካባቢውን የማስተዳደር ኃላፊነት" እንደወሰዱም ገልጿል።

በአላማጣ ከተማ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም ሰለሞን አያሌው በተባሉ ባለሀብት ቤተሰብ ላይ በደረሰ ጥቃት የሁለት ልጆች ሕይወት ሲያልፍ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታ ለቢቢሲ ይህ ክስተት የመጀመሪያ እንዳልሆነ ተናግረው፣ የታጠቁ ሰዎች በከተማዋ ተደጋጋሚ አፈና እና ግድያ እየፈጸሙ ነው ብሏል።

በዕለቱ ታጣቂዎቹ የአቶ ሰለሞን አያሌው መኖሪያ ቤት አጥር ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ ጥሰው በመግባት "በጥይት እና በቦምብ ድንገተኛ ጥቃት ፈጸመዋል" ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።

ነገር ግን የከተማው የፀጥታ ኃይሎች ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለ30 ደቂቃ ያህል የቆየ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ተናግረዋል።

የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣው መግለጫ በደቡብ ትግራይ እና ደቡብ ምሥራቅ ዞኖች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ እና ሁከትም በመጥቀስ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ባለፈው ሳምንት በክልሉ የአመራር ለውጥ መደረጉን ካወጁ በኋላ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሕዝባዊ ተቃውሞ ተደርጓል።

ተቃውሞው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ ሲሆን፣ ሰልፈኞቹ በትጥቅ የተካሄደውን የአስተዳደር ለውጥ በማውገዝ "ለህወሓት አንገዛም" የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል።