በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ስለተከሰተው ግጭት እስካሁን የምናውቀው

በአፋር ክልል መቀመጫቸውን ያደረጉት የትግራይ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, SM

ከትግራይ ኃይሎች ተለይተው በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው 'የትግራይ የሰላም ኃይል' ታጣቂዎች ከቀናት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ትግራይ ዘልቀው በመግባት ጥቃት በመፈጸም በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ነሐሴ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከአፋር ክልል በተነሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ትንኮሳ መፈጸሙን በመግለጽ በጥቃቱ አንድ የፀጥታ አባል መገደሉን ገልጿል።

የአፋር እና የትግራይ ድንበር አዋሳኝ አካባቢ ተፈጠረ በተባለው ግጭት ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ነው።

ቅዳሜ ዕለት የተፈጸመው ይህ ጥቃት በማኅበራዊ ድረገፆች ላይ መነጋገሪያ የነበረ ሲሆን፣ ቢቢሲ ትግርኛ የታጣቂዎቹን አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ገ/እግዚአብሐር በየነ ስለክስተቱ ማብራሪያ ጠይቋል።

ጄነራሉ "እንዲፈጠር ያልፈለግነው ግጭት ነው የተፈጠረው። ምክንያቱም በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል ነው ግጭቱ እየተካሄደ ያለው" በማለት ግማሽ ሰዓት ያህል የቆየ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተናግረዋል።

የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በመግለጫው ላይ "ለሁለተኛ ጊዜ ከአፋር ክልል ልዩ ቦታው ጠብጣብ ተነስተው ደደርባ በተባለ አካባቢ ያለው ኃይል ላይ በከፈቱት ተኩስ አንድ ታጋይ መስዋዕት ሆኗል" ብሏል።

የታጣቂዎቹ አዛዥ የሆኑት ብ/ጄነራል ገ/እግዚአብሐር በበኩላቸው "ሁኔታው ወደ ግጭት እንዲያመራ አንፈልግም ነበር። ለዚያም ነው ወደ አፋር በረሃ ወርደን ሀሩር እያቃጠለን ያለው። ይህም ሆኖ ግን ድንበር ዘለው ወደ አፋር ክልል በመግባት ነው ከብበውን ተኩስ የከፈቱብን" ሲሉ የክልሉ መግለጫ ያስተባበሉት።

ከአንድ ወር በፊት ወደ ደቡብ ምስራቅ ዞን ትግራይ ተንቀሳቅሰው ለአጭር ጊዜ የቆየ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ያስታወሱት ጄነራሉ፣ "ሕዝቡ በእርሻ ወቅት ውጊያ አትክፈቱብን። እናሸማግላችሁ" እንዳላቸው በመጥቀስ የታጣቂዎቹ አዛዥ "ቃላችንን አክብረን" ወደ አፋር ተመልሰናል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ የትግራይን ድንበር አልፈው በመግባት ጥቃት የከፈቱት በአፋር መቀመጫቸውን ያደረጉ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጾ ነበር።

ቢሮው ታጣቂ ቡድኑ ይህ አጥፊ ተግባር ከቀጠለ በሚመሩት እና በሚያስተባብሩ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ በማለት አስጠንቅቆ ደም መፋሰሱ በአስቸኳይ ይቁም በማለት ጥሪ አድርጓል።

ብ/ጄነራል ገ/እግዚአብሐር ግን የትግራይ ኃይሎች "በዕለቱ እንደሚመጡ እናውቅ ነበር" በማለት ታጣቂዎቹ እርስ በርስ እንደሚተዋወቁ እና አፋር ክልል ዘልቀው በመግባት ከበባ ከፈጸሙ በኋላም "ተዉ አትጠጉን" በማለት እንደለመኗቸው ይናገራሉ።

"ዝም ብለህ እጅ ስጥ እያሉ ይሳደቡ ነበር። በግራ እና በቀኝ ተጠግተው ዲሽቃ እና ብሬል ተኮሱብን። ከዚያ በኋላ የግማሽ ሰዓት ተኩስ ተካሄደ። የጨበጣ ውጊያም ተካሂዷል" ብለዋል።

ግጭቱ አጋጥሞበታል የተባለው ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰነው የአፋር ክልል አካባቢን በተመለከተ ክልሉ ያለው ነገር የለም።

ብ/ጄነራሉ የትግራይ ኃይሎች የተነሱት ዳንደ ከሚባል አካባቢ መሆኑን ገልጸው ከሦስት አርሚዎች የተውጣጡ መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

"እነርሱ ናቸው ማጥቃት የጀመሩት የሚለው ሐሰት ነው። ተኩስ የከፈቱበት አካባቢ ውሃ አለ። ውሃው የት ነው ያለው ብላችሁ መጥታችሁ ማየት ትችላላችሁ" ሲሉ የትግራይ ክልል ያወጣውን መግለጫ አስተባብለዋል።

"በሞተው አባል እናዝናለን" የሚሉት ጄነራሉ በግጭቱ ያጋጠመውን ሞት "የጋራ ኪሳራ ነው" ብለዋል።

አክለውም ". . .የተሰዉትም የቀሩትም ታጋዮቻችን ናቸው። የትግራይ ኃይል ተገድዶ የሚዋጋ እንጂ የለውጥ ኃይል ነው። አባላችን እንደተሰዋ አድርገን ነው የምንቆጥረው" ብለዋል።

የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ራሳቸውን የትግራይ ሰላም ኃይል በማለት የሚጠሩት እና በአፋር በረሃ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎችን በፌደራል መንግሥቱ ይደገፋሉ ሲሉ ይወነጅሏቸዋል።

ትግራይ ክልል ከአፋር ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ የሚነገርላቸው እና በተለምዶ "ሓራ መሬት" (የነጻ መሬት ተዋጊዎች) ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች፣ በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ ከትግራይ ኃይሎች ተነጥለው የወጡ ናቸው።

እነዚህ ታጣቂዎች በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ እና ድርጅቱን የሚደግፉ የትግራይ ኃይሎች አዛዦችን ከሥልጣን ለማስወገድ ወደ አፋር ክልል ሄደው መደራጀታቸውን ይናገራሉ።

የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያበቃው የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ በትግራይ ተቋቁሞ የነበረው በአቶ ጌታቸው ረዳ የተመራውን ጊዜያዊ አስተዳደር በሚደግፉ እና በህወሓት ሊቀምንበር በሚመሩት የድርጅቱ አባላት መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ይታወቃል።

በዚህም ምክንያት በርካታ የትግራይ ኃይሎችን የሚመሩ ወታደራዊ መኮንኖች በምርጫ ቦርድ ሕጋዊነቱ የተሰረዘበትን ህወሓት የሚመሩትን ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤልን ደግፈው ሲቆሙ፤ ሌሎች ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ተቃውሞ በማሰማት ከቡድኑ ተለይተዋል።