ሰኞ ምሽት በአላማጣ ከተማ የተፈጠረው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Alamata comm.
በአላማጣ ከተማ ሰኞ ጳጉሜ 3/2017 ዓ.ም. በነበረ የተኩስ ልውውጥ የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፤ በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች የተኩስ ልውውጡ በትግራይ ታጣቂዎች እና በፌደራል የፀጥታ አካላት መካከል መሆኑን ገልጸዋል።
በቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሾሙት እና አሁን ከኃላፊነታቸው የተነሱት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታ ክስተቱ መፈጠሩን አረጋግጠው፣ ነገር ግን "አፈሙዝ የያዙ" ያሏቸው የህወሓት ታጣቂዎች በፈጠሩት የፖለቲካ ሁኔታ በአካባቢው ባለመኖራቸው ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ እንዳስረዳው ከሆነ በከተማዋ የተኩስ ልውውጡ የተፈጠረው ጳጉሜ 3/2017 ዓ.ም. ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት መካከል ነበር።
"አብዛኛው ሕዝብ ተኝቶ ስለ ነበር" ምን እንደተፈጠረ ማጣራት የተቻለው ከነጋ በኋላ ማክሰኞ ጳጉሜ 4 መሆኑንም አስረድቷል።
ለግጭቱ መንስዔ የሆነው በአማራ ብልጽግና የተሠራ ያሉትን "ወንጭፍ አደባባይ" በማፍረስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማን አውርዶ፣ የትግራይ ክልል ባንዲራን ለመስቀል በሚሞክሩበት ወቅት መሆኑንም ጨምሮ ተናግሯል።
የአካባቢው ነዋሪ ለፌደራልም ለኮማንድ ፖስቱም አደባባዩን ለመሥራት ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ፈቃድ አለማግኘቱን የገለፀው ይህ ነዋሪ፣ በቅርቡም የትግራይ ኃይሎች ሁለት የከተማዋን ቀበሌዎች መቆጣጠራቸውን ገልጿል።
በ"ወንጭፍ አደባባይ" ላይ ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀል በመሞከር ሂደት ውስጥ በትግራይ እና በፌደራሉ ኃይሎች መካከል ግጭት ሲከሰት አንድ የፌደራል አባል በተኩስ መገደሉን መስማቱንም ገልጿል።
ከዚያ በኋላ ግን ውጥረቱ ተባብሶ በመቀጠሉ የመከላከያ አባላት ወደ ስፍራው ከመጡ በኋላ በተፈጠረ ተኩስ ሰባት ይደርሳሉ የተባሉ የትግራይ ኃይሎች አባላት መገደላቸውን ተናግሯል።
ቢቢሲ የሟቾቹን ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ከዚህ በኋላ የተቆጡ የትግራይ ኃይሎች በአካባቢው የሚገኝ የመሐመድ ሉህሉህ ሕንጻ ውስጥ በመግባት "ቤንዚን አርከፍክፈው" በማቃጠል ጉዳት ማድረሳቸውን እና አራት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
በአካባቢው የፌደራልም ሆነ የመከላከያ ኃይሎች እንደሚገኙ የሚናገሩት ነዋሪዎች የትግራይ ኃይሎች ግን ወደ ስፍራው በመምጣት የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎችን ቀበሌ 02 እና 03 የሚባሉ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ይናገራሉ።
"ይህ ሁሉ ሲሆን መከላከያ ምንም አላደረጋቸውም" የሚሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ነዋሪ ይህም በሕዝቡ ውስጥ ፍርሃት መፍጠሩን ያስረዳሉ።
የመሐመድ ሉህሉህ ሕንጻ ላይ የነበሩ አራት የሞባይል መሸጫዎች፣ በርገር ቤት እንዲሁም ቡቲኮች በቃጠሎው መውደማቸውን ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልፀዋል።
"የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ከገቡ ጀምሮ በሕዝቡ ላይ ብዙ ግፍ ፈጽመዋል" ያሉ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው በመከላከያ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የነበረው የተኩስ ልውውጥ "ለ30 ደቂቃ ያህል የቆየ" እንደነበር ተናግረዋል።
እኚህ ነዋሪ ታጣቂዎቹ የ02 እነ የ03 አካባቢን መቆጣጠራቸውን አረጋግጠው አራት ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ምሽትም ጫት ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በከፈቱት ተኩስ አንድ ሰው ማቁሰላቸውን ገልፀዋል።
"ከሞቱት መካከል አንደኛው ማቻሬ ከሚባል ቦታ ተነስቶ ወደ ሳዑዲ ለመሄድ የመጣ መንገደኛ ነው" ያሉት ግለሰቡ፣ሁለቱ የተቃጠለው ሕንጻ ላይ ልብስ ስፌት የሚሠሩ ልጆች እንደነበሩ አስረድተዋል።
የህወሓት ታጣቂዎች በተኩስ ልውውጡ መሞታቸውን መስማታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
የአካባቢው ነዋሪ በተፈጠረው ሁኔታ ተደናግጦ ማክሰኞ ከቤቱ ሳይወጣ ማሳለፉን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ረቡዕ ዕለትም መጠነኛ እንቅስቃሴ ብቻ እንደነበር ይናገራሉ።
በቅርቡ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የከተማዋ ከንቲባ ተደርገው መሾማቸውን የሚናገሩት አቶ ሞገስ ሽፈራው በበኩላቸው ጳጉሜ 3 2017 ዓ.ም. በከተማዋ ላይ የተኩስ ልውውጥ ነበረ መባሉን አስተባብለዋል።
ጳጉሜ 3 ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ አራት የትግራይ የፀጥታ ኃይል አባላት "ማዞሪያ" በሚባል አካባቢ በእግራቸው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ተኩስ አንደተከፈተባቸው በመግለጽ የነዋሪዎቹን እና የቀድሞውን ከንቲባ አስተያየት ውድቅ ያደርጋሉ።
"የፌደራል እና የመከላከያ ኃይል አባላት ቁሙ አሏቸው። ምን ስላጠፋን ነው ቁሙ የምትሉን በማለት መንገዳቸውን ቀጠሉ። ቀጥታ በሕንጻው እና በምድር ላይ የነበሩ ከ200 በላይ የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፈቱባቸው፤ አጋጣሚ የፍሳሽ መሄጃ ቱቦ ውስጥ ዘልለው በመግባት ሕይወታቸውን አድነዋል።"
አቶ ሞገስ ሽፈራው አክለውም "ከእኛ ወገን [ከትግራይ የፀጥታ ኃይሎች] የተተኮሰ ጥይት የለም" ሲሉ አስተባብለዋል።
ቢቢሲ የከተማውን ፀጥታ እንዲቆጣጠጠር ኃላፊነት ከተሰጠው የኮማንድ ፖስት ስለጉዳዩ ያገኘው መረጃ የለም።
ከንቲባ ሞገስ ግን በሁለት ወገን የተኩስ ልውውጥ አልነበረም በማለት እንቅስቃሴ ላይ በነበሩ የትግራይ የፀጥታ ኃይል አባላት ላይ "ጥቃት ተፈጽሟል" ሲሉ ወንጅለዋል።
"ፎቅ ላይ የነበረ አካል ቦንብ ወረወረ። ያ ቦንብ አየር ላይ እያለ ስለፈነዳ በግለሰብ ንብረት ላይ ውድመት ደርሷል፤ ሦስት ንጹኃን ዜጎችም ሞተዋል። ከእኛ ወገን የተተኮሰ ነገር የለም።"
"ሕንጻው መሐመድ ሳኒ የተባለ ግለሰብ ሲሆን የተለያዩ ንግዶች የሚካሄድበት የገበያ ማዕከል ነው" በማለት ሕንጻው ላይ እና ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል።
አክለውም በቦምብ ፍንጣሪ "ከአራቱ የትግራይ የፀጥታ አባላት ሁለቱ ቆስለዋል። ከሞቱት ደግሞ ሁለቱ ሕንጻው ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሲሆን አንዱ መንገደኛ ነው" ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞው የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳደርን በማፍረስ አዳዲስ አመራሮችን መሾሙ ይታወሳል።
ይህም በስፍራው ውጥረት የፈጠረ ሲሆን ሕዝባዊ ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ የደቡብ ትግራይን አስተዳደር በአዲስ ለመተካት ያደረገው ሙከራ ተቃውሞ ገጥሞታል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ነባሩ የደቡባዊ ዞን አስተዳደር ከሥልጣን ወርዶ በአዳዲስ ተሿሚዎች እንደሚተካ ውሳኔያቸውን ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም. ባስታወቁበት ወቅት "በቀጣይ ሊከተሉ የሚችሉ አደጋዎችን ለማስቀረት" ያለመ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
ይሁን እንጂ የትግራይ ኃይሎች የከተማዋን የተለያዩ ቢሮዎች በኃይል መቆጣጣራቸው የተሰማ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ በተለያየ ወቅት በተፈጠሩ አለመግባባቶች የሰላማዊ ዜጎች ሕይወት አልፏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሰኞ ዕለት በአካባቢው ስለተፈጠረው ግችር እና ስላላፈው የሰው ሕይወት እስካሁን ያለው ነገር የለም።















