ብሪታኒያውያን የማኅበራዊ ሚድያ አክቲቪስቶች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ተከለከሉ

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ሁለት ብሪታኒያዊን አክቲቪስቶችን ጨምሮ አምስት ሰዎች የንግግር ነፃነትን "ለማፈን" ሞክረዋል በሚል ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸው ተሰማ።
የሌበር ፓርቲ የቀድሞ አማካሪና ሴንተር ፎር ካውንተሪንግ ዲጂታል ሄት የተሰኘ ማዕከል መሪ የሆነው ኢምራን አሕመድ እና የግሎባል ዲስኢንፎርሜሽን ኢንዴክስ ኃላፊዋ ክሌር ሜድፈርድ በትራምፕ አስተዳደር "ፅንፈኛ አክቲቪስቶች" ተብለው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
ፈረንሳዊው የአውሮፓ ኅብረት የቀድሞ ከፍተኛ ኮሚሽነር እንዲሁም ሁለት ጀርመን የሚገኙ ነባር የፀረ-ኦንላይን ጥላቻ አራማጆችም አሜሪካ መግባት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።
የአውሮፓ መሪዎች እርምጃውን የተቃወሙት ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ደግሞ የንግግር ነፃነት ለማስጠበቅ "ቁርጠኛ" እንደሆነ አስታውቋል።
"እያንዳንዱ አገር የራሱ የቪዛ መመሪያ እንዳለው ብንገነዘብም ኢንተርኔትን ከጎጂ ይዘት የሚጠብቁ ሕግጋትን እና ተቋማትን እንደግፋለን" ይላል የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ መግለጫ።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን የጉዞ እገዳውን "የአውሮፓ ዲጂታል ነፃነት ላይ የተቃጣ ማስፈራራት እና ማፈን ነው" ብለውታል።
የአውሮፓ ኅብረት ውጭ ጉዳይ ኃላፊ ካጃ ካላስ በበኩላቸው "ተቀባይነት የሌለውና ነፃነታችንን ለመገዳደር የተደረገ ሙከራ ነው" ብለዋል።
አሜሪካ እርምጃው የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ገደብ እንዲበጅላቸው ዘመቻ ያደረጉ ሰዎች እና ተቋማት ላይ የተወሰደ ነው ብላለች።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ "ፕሬዝደንት ትራምፕ የአሜሪካን ሉዐላዊነት የሚጥሱ የውጭ ፖሊሲዎችን እንደማይቀበሉ ገልፅ አድርገዋል። የአሜሪካ የንግግር ነፃነትን ለማፈን የሚሞክሩ ሰዎችም ተቀባይነት የላቸውም" ብለዋል።
ከሌበር ፓርቲ ጋር ቅርበት ያለው አሕመድ ከባይደን አስተዳደር ጋር በቅርበት ይሰራ የነበረ ነው ስትል አሜሪካ ትኮንናለች። ቢቢሲ የአሕመድን ተቋም አስተያየት ጠይቋል።
ክሌር ሜልፈርድ ደግሞ የተሳሳተ መረጃን ስርጭትን ለመቆጣጠር ጂዲአይ የተሰኘውን ድርጅት ያቋቋመቸው በ2018 ነበር።
የጂዲአይ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደገለፁት "የቪዛ ክልከላው የንግግር ነፃነት ላይ የተቃጣ ጥቃት እና የመንግሥትን ሳንሱር የሚያሳይ ነው።"
"የትራምፕ አስተዳደር የሚቃወመውን ድምፅ ለማፈን እና ለማስፈራራት የፌዴራል መንግሥቱን እየተጠቀመ ነው። የዛሬው እርምጃቸው ሞራል የጎደለው፣ ሕጋዊ ያልሆነ እና አሜሪካዊያን ያልተላበሰ ነው።"
በአውሮፓ ኅብረት የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ከፍተኛ ኮሚሽነር የነበሩት ቲየሪ ብሬቶን ቪዛ ከተከለከሉ ግለሰቦች መካከል ናቸው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሬቶን የአውሮፓ ኅብረት ዲጂታል ሰርቪስስ አክት "አድራጊና ፈጣሪ" ናቸው ሲል ገለጿቸዋል። ድርጅቱ ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ነው።
ብሬቶን ከኤክስ ባለቤቱና ከዓለማችን ቱጃሩ ሰው ኢላን መስክ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ያውቃሉ።
የአውሮፓ ኮሚሽን በቅርቡ በሰማያዊ እርማት (ብሉ ቲክ) ሳቢያ ኤክስን 120 ሚሊዮን ዩሮ መቅጣቱ ይታወሳል። ኅብረቱ እንደሚለው ኤክስ የተጠቃሚዎችን ማንነት "በደንብ ሳያጣራ ነው" ብሉ ቲክ የሚሰጠው።
የቪዛ እገዳውን ተከትሎ አስተያየቻውን በኤክስ ገፃቸውን የሰጡት ብሬቶን "አሜሪካዊያን ወንድሞቻችን ሳንሱር ያለው የምታስቡት አይደለም" ብለዋል።















