አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአገራት ጋር እየተፈራረመችው ያለው ስምምነት ለምን አነጋጋሪ ሆነ?

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ እና አምባሳደር ማሲንጋ

የፎቶው ባለመብት, MOH/FB

የምስሉ መግለጫ, የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ እና አምባሳደር ማሲንጋ

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ አሜሪካ በግዙፉ የተራድኦ ተቋሟ ዩኤስኤይዲ በኩል ከተለያዩ አገራት የነበራትን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እና ትብብር አቋርጣለች። በምትኩም፤ በተለይ በጤናው መስክ አዲስ አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች።

'አሜሪካ ፈርስት ግሎባል ሄልዝ ስትራቴጂ' የተባለው ይህ አዲስ ዕቅድ ዓለም አቀፍ የጤና ፖሊሲን ከውጭ እርዳታ ጋር አጣምሯል። ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ስትራቴጂው ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል ስምምነት ከአገራት ጋር እየተፈረመ ነው።

አዲሱ አቀራረብ ቀደም ሲል ለአገራት ሲሰጥ የቆየውን መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በኩል ሲያካሂድ የነበረውን የእርዳታ አቅርቦት እና አሠራር ሙሉ በሙሉ ቀይሯል። የሚከናወነውም ከመንግሥታት ጋር በሚደረግ ጥምረት እና በሚፈረም ስምምነት አማካኝነት ነው።

ባለፈው መስከረም ወር በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይፋ የተደረገው ይህ 'ቅድሚያ ለአሜሪካ' የተሰኘው ዓለም አቀፍ የጤና ስትራቴጂ ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ የሁለትዮሽ አጋርነትን መሠረት ያደረገ፣ እንዲሁም አጋር አገራትም የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።

ባለፉት ሳምንታት የአሜሪካ መንግሥት ከተለያዩ አገራት ጋር እየተፈራረመ ካለው ስምምነት ውስጥ አንዱ የሆነውን አጋርነት ከኢትዮጵያ ጋር ተፈራርሟል።

ለአምስት ዓመታት የሚቆየው በዚህ ስምምነት አማካኝነት ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በጤና ዘርፉ ላይ ፈሰስ ይደረጋል። የአሜሪካ መንግሥት 1.16 ቢሊየን ዶላር የሚሆነውን ሲሸፍን፣ የተቀረው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሚሸፈን ይሆናል።

ይህንን ስምምነት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በመፈራረም ቀዳሚ የሆነችው ጎረቤት አገር ኬንያ ናት። ኬንያ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ስምምነትን በፕሬዝዳንቷ እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አማካኝነት በኅዳር ወር መጨረሻ ላይ ተፈራርማለች።

ስትራቴጂው ከአገራት ጋር የሚደረገው ስምምነት እንደ ሰብዓዊ እርዳታ አይመለከትም። ይልቁንም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚከሰቱ በሽታዎችን ባሉበት ቀድሞ በመለየት፣ በመከላከል እና በመቆጣጠር የአሜሪካውያንን ደኅንነት መጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዕቅዱ ትራምፕ ሲወቅሱት የቆዩትን የዓለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማትን እንዲሁም በአሜሪካ መንግሥት ሥር የነበሩትን ዩኤስኤአይዲን እና ፔፕፋርን በገንዘብ በመደገፍ ሥራዎችን እንዲያካሂዱ ከማድረግ ይልቅ በአሜሪካ እና በመንግሥታት መካከል በሚደረስ ስምምነት በጋራ በሚመደብ ገንዘብ የሚከናወን ይሆናል።

ሂደቱ በቀጥታ ተጠቃሚዎችን ከማግኘት ይልቅ ከመንግሥታት ጋር በሚደረግ ትብብር ላይ ያተኩራል።

ትብብሮቹ ዓላማዎች አንዱ የአገራትን በሽታዎችን ቀድሞ የመለየት አቅምን በማጠናከር ወደ አሜሪካ ሳይደርሱ በቁጥጥር ስር ማዋል ነው። በሌሎች አገራት ውስጥ ያሉ የጤና ሥርዓቶችን በማጠናከር ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግም ይጠቀሳል።

ነገር ግን ይህ ስትራቴጂ ትችቶች እየቀረቡበት ነው። ባለሙያዎች እንደሚሉት ለውጡ በሥራ ላይ ያለውን ዓለም አቀፋዊ የጤና ሥርዓትን ያዳክማል፣ አስፈላጊ አገልግሎቶችንም ያስቀራል። በተጨማሪም ቀደም ሲል የተከሰቱ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር ያስቻለውን የዘርፈ ብዙ ትብብር ማዕቀፍ ይጎዳል የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

በአፍሪካ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አገራት ከአሜሪካ ጋር እየተፈራረሙ ባለው የሁለትዮች ስምምነት ላይ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው።

ፍትሐዊ የጥቅም ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ብሔራዊ የጤና እና ናሙናዎች የማጋራት ስምምነት ላይ መድረስ አገራት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ያሳጣል በማለት ይከራከራሉ።

እንዲሁም ይህ በአሜሪካ እና በአገራት መካከል የሚደረሰው ስምምነት ብሔራዊ እና ቀጠናዊ የጤና መረጃ ሉዓላዊነትን የሚሸረሽር እንዲሁም በድርድር የሚደረሰውን አህጉራዊ ማዕቀፍንም የሚያዳክም ነው ይላሉ።

አገራት ከአሜሪካ ጋር በሚደርሱት ስምምነት የጤና መረጃ አያያዝ ሥርዓታቸውን የማጠናከር ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን፣ ለዚህም የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ፈራሚ አገራት የጤና መሠረተ ልማቶቻቸው አኳያ በውጭ አገራት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ፕሬዚዳንት ሩቶ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙዳቫዲ እና ሩቢዮ የአገሮቻቸው ሰንደቅ ዓላማ ከኋላቸው ይታያል

የፎቶው ባለመብት, @WilliamsRuto/X

የምስሉ መግለጫ, በኬንያ እና በአሜሪካ መካከል ስምምነቱ የተፈረመው ዋሺንተግን ውስጥ ነበር

በኬንያ በፍርድ ቤት የታገደው ስምምነት

ይህንን ስምምነት በመፈረም ቀዳሚዋ አገር የሆነችው ኬንያ በአምስት ዓመታት ውስጥ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍን ታገኛለች። የስምምነቱ መፈረም አሜሪካ ምሥጢራዊነት ያላቸውን ግላዊ የጤና መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት ያስችላታል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

አንዳንድ ኬንያውያን ይህ ስምምነት ዩናይትድ ስቴትስ እንደ የኤችአይቪ፣ የቲቢ ሕክምና ታሪክ እና የኬንያውያንን የክትባት መረጃዎችን የመሳሰሉ የግል የሕክምና መረጃዎችን እንድታገኝ ያደርጋታል በሚል ስጋት ሙሉ የስምምነቱ ይዘት እንዲገለጽ እየጠየቁ ነው።

"ለአሜሪካ እንዲጋሩ የሚደረጉት ምን ዓይነት ልዩ የመረጃ ምድቦች ናቸው? የዘረ መል መረጃ፣ የበሽታ ክስተት ሁኔታ፣ የአእምሮ ጤና መረጃዎች፣ የኢንሹራንስ ክፍያ ጥያቄዎች፣ የሆስፒታል መዛግብት ወይም ባዮሜትሪክስ? እነዚህን የሚያካትት ካልሆነ ለምን በግልጽ አልተጻፈም?" በማለት ጠበቃ ዊሊስ ኦቲኖ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ስጋት የገባቸው በርካታ ኬንያውያንም መንግሥታቸው ከአሜሪካ ጋር የተፈራረመውን ሙሉውን የስምምነቱን ይዘት ለሕዝብ እንዲገለጽ በጠየቁት መሠረት ይፋ ተደርጓል።

ስምምነቱ ከተፈረመ ከሳምንት በኋላ የኬንያ ፍርድ ቤት የግላዊ መረጃ ደኅንነት ጥበቃን በተመለከተ ለዜጎች መብት የሚከራከሩ ቡድኖች ባቀረቡት አቤቱታ ምክንያት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን አግዷል።

ፍርድ ቤቱ በውሳኔው በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ጥበቃን የሚፈልጉ የጤና መረጃዎች ተላልፈው እንዳይሰጡ ጊዜያዊ ዕግድ ጥሏል።

የኬንያ መንግሥትም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብር እና ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጾ፣ ዕገዳው በሙሉ ስምምነቱ ላይ ሳይሆን መረጃ ማጋራትን በሚመለከተው ክፍል ላይ ብቻ መሆኑን አብራርቷል።

ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከወሰዱት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የኬንያ ሸማቾች ፌዴሬሽን፤ አገሪቱ ወሳኝ የሆኑ የጤና ሥርዓት መረጃዎችን አሳልፋ በመስጠት በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ስጋት ተደቅኗል ብሏል።

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ የካቲት መጀመሪያ ሳምንት ድረስ የሚቆይ ዕገዳ በስምምነቱ ላይ የጣለው ጉዳዩ ሙሉ ለሙሉ እስኪሰማ እና ዘላቂ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኬንያ መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን ስጋት ለማረጋጋት ምላሽ ሰጥቷል። የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ ተገቢውን አሠራር በመከተል፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የመረጃ ባለቤትነት እና የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሙሉ ለሙሉ በተከበረበት ሁኔታ መከናወኑን አመልክቷል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ጋር ስምምነቱን እየተፈራረመች ነው። እስካሁንም ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ዩጋንዳ፣ ሌሶቶ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሞዛምቢክ ካሜሩን እና ናይጄሪያ ከአሜሪካ ጋር የመግባቢያ ሰነዱን በመፈረም የተለያየ መጠን ያለው ድጋፍን ለማግኘት ተስማምተዋል።

አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) እንደዘገበው ስምምነቱን ከፈረሙት አገራት መካከል የተወሰኑት አሜሪካ ትሰጠው የነበረው ድጋፍ የቀነሰባቸው ናቸው። አልያም ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የሚባረሩ የሦስተኛ አገር ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምተዋል።

ለዚህም እንደማሳያ ናይጄሪያ በስምምነቱ ለአምስት ዓመታት ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት "ክርስቲያኖችን ከጥቃት ለመጠበቅ በምትሰጠው ትኩረት እና ለክርስቲያን የጤና ተቋማት ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ" በመስማማቷ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጠቅሷል።

ስምምነቱ የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ አገራት ከአሜሪካ ጥቅም ጋር የማይስማማ ፕሮግራም የሚያካሂዱ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ ስምምነቱ እንዲቋረጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, MOH/FB

ኢትዮጵያ የፈረመችው ስምምነት

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ስምምነቱን መፈረሟ የተገለጸው ማክሰኞ ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም. ሲሆን ከኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ ከአሜሪካ በኩል ደግሞ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ከስምምነቱ በኋላ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል በሚደረገው ስምምነት አማካኝነት ለአምስት ዓመታት 1.6 ቢሊየን ዶላር በጤና መስኩ ላይ እንደሚውል ተገልጿል።

የስምምነቱ ዝርዝር ይዘት እስካሁን የታወቀ ባይሆንም በመሠረታዊ ይዘት ግን አሜሪካ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ከፈረመችው ስምምነት የተለየ እንደማይሆን ይታመናል። ስለዚህም አነጋጋሪ የሆነው የጤና መረጃ ማጋራት ጉዳይ ሊነሳ ይችላል።

ከዚህ አንጻር ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ የኢትዮጵያ የግል መረጃ ጥበቃ ሕግ ነው የሚሆነው። በእርግጥም ኢትዮጵያ በፈረመችው ስምምነት ውስጥ የመረጃ ማጋራት ጉዳይ የሚኖር ከሆነ በ2016 ዓ.ም. የወጣው "የግል ዳታ ጥበቃን አዋጅ" የሚነሳ ይሆናል።

ከዚህ አኳያ በአንቀጽ 20 ላይ ዳታ ከአገር ውስጥ ወደ ውጪ አገር የሚተላለፍባቸው ሁኔታዎች በተዘረዘረበት ክፍል ውስጥ የግል ዳታ (መረጃ) ደኅንነትን እና ጥበቃን ለማረጋገጥ የተዘረዘሩ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው እና የሚመለከተው ባለሥልጣን ሲወስን መሆኑ ተጠቅሷል።

አሜሪካ ከሌሎች አገራት ጋር ባደረገችው ስምምነት ውስጥ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያግዙ መረጃዎች መለዋወጥን እንደሚመለከት በመነሳቱ በተለይ ኬንያ ውስጥ ከፍተኛ ጥያቄ ማስነሳቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ ያደረገው ጥበቃ የሚደረግላቸው ግላዊ መረጃዎች ይካተታሉ በሚል ስጋት ነው።

በኢትዮጵያ የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ውስጥም እነዚህ ግላዊ መረጃዎች "ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል ዳታ" በማለት የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህም የትኞቹን ግላዊ መረጃዎችን እንደሚያካትት በግልጽ ተጠቅሷል።

አገራት እየደረሱት ካለው ስምምነት አንጻር ስንመለከት ጥንቃቄ የሚደረግላቸው የግል መረጃዎች የሚባሉት የአንድ የተፈጥሮ ሰው ዘርን ወይም ብሔርን፣ የዘረመል ወይም የማንነት አካላዊ ዳታን፣ የአካላዊ ወይም የአእምሯዊ ጤንነት ወይም ሁኔታን እና ሌሎችንም የሚያካትት ነው።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በደረሰችው ስምምነት ይህ የመረጃ መጋራት ሁኔታ ስለመኖሩ እስካሁን የተባለ ነገር የለም። የሚኖርም ከሆነ ለምን አገልግሎት እንደሚውል እና ምን ዓይነት ጥበቃ እንደሚደረግለት ወደፊት የሚታወቅ ይሆናል።